በህብረተሰብ ተሳትፎ በመንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑት ድርጅቶች የተገነቡ ፕሮጀክቶችን በመንከባከብ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የዲላ ከተማ አስተዳደር አሳሰበ።
ይህ የተገለፀው በዲላ ከተማ ጪጩ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት የተገነቡ አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎች በተመረቁበት ወቅት ነው።
በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የዲላ ከተማ ከንቲባ አቶ ብዙአየሁ ታደሰ፤ ምቹ የመማሪያ ስፍራ መፍጠር የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑን አንስተው፤ ይህን ከመደገፍ አንፃር የከተማ ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮጀክት ያከናወነው ተግባር ለሌሎች አርአያ የሚሆን ነው ብለዋል።
በትምህርት ዘርፍ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የትምህርት አመራርና ወላጆች በህብረተሰብ ተሳትፎ፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የተገነቡ ፕሮጀክቶችን በመንከባከብ የበኩላቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ሥራ ፕሮጀክት ኃላፊ አቶ ገልገሎ ገዛኸኝ በበኩላቸው፤ የመሠረተ ልማት ችግር ያሉባቸውን አካባቢዎች ለይቶ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።
ለምረቃ የበቁት መማሪያ ክፍሎች ለተማሪዎች ምቹ የመማሪያ ስፍራ ይፈጥራል ያሉት ኃላፊው ፤ በቀጣይ የሕብረተሰቡን ተሳትፎ በማጠናከር በትምህርት ቤቱ የሚስተዋሉ ሌሎች የመሠረተ ልማት ክፍተቶችን ለማሟላት በቅንጅት እንደሚሠራ ጠቅሰዋል።
የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ከሚከናወኑ ተግባራት ቅድሚያ የሚሰጠው ደረጃቸውን የጠበቁ የመማሪያ ክፍሎችን መገንባት መሆኑን የጠቆሙት ደግሞ የዲላ ከተማ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ግርማ ዶሪ (ዶ/ር) ናቸው።
የተገነቡ የመማሪያ ክፍሎች የነበረውን የክፍል ጥበት በመቅረፍ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በትኩረት እንዲከታተሉ እንደሚያግዙና በተማሪዎች ውጤት መሻሻል ላይ ጉልህ አበርክቶ እንደሚኖራቸው ኃላፊው አብራርተዋል።
የዲላ ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ ተፈሪ በበኩላቸው፤ ልማታዊ የሴፍትኔት ፕሮግራም በከፋ የኑሮ ደረጃ ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን በመደገፍና የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በመገንባት የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም መሰል የልማት ተግባራትን በማስፋፋት ዜጎችን ከተረጂነት በማላቀቅና የከተማውን የልማት ጉዞ ለማፋጠን ትኩረት ሰጥተው እንደሚንቀሳቀሱ ገልፀዋል።
የዲላ ከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ኃላፊ አቶ የኋላእሸት ለማ እንደገለፁት፤ ፕሮጀክቱ ከሚሰጣቸው ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች መካከል ዜጎችን ከድህነት ለማላቀቅ መሠረታዊ ፍላጎቶች ላይ በማተኮር ተምረውና ሠርተው ሕይወታቸውን እንዲያሻሽሉ ድጋፍና ክትትል ማድረግ ዋነኛው ተግባር ነው ብለዋል።
ትምህርት የዕድገት መሰረት በመሆኑ ፕሮጀክቱ ለዘርፉ ትኩረት መስጠቱን ገልፀው፤ ተገንብተው ለምረቃ የበቁ መማሪያ ክፍሎች ከዚህ ቀደም ይስተዋል የነበረውን የክፍል እጥረት በመቀነስ የመማር ማስተማር ሂደቱን ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክትም ገልፀዋል።
ዘጋቢ፡ ውብሸት ኃ/ማርያም – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
ወጣቶች ሚዲያ ሲጠቀሙ ከፋፋይ ከሆነ አጀንዳ በመውጣት የማህበረሰቡን አንድነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ሊያተኩሩ ሊገባል
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን መከበሩ ቱባ ባህሎችን ለማስተዋወቅ አስተዋፅኦ አለው – የኮሬ ዞን ምክር ቤት
የመንግስታዊ አገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያ ሪፎርም ትግበራ መጀመሩን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ