ብዙ ያልተወራለት የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ

ብዙ ያልተወራለት የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ

የተፈጥሮ ውበቷ የማይነጥፈው ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ ከታደለቻቸው ፀጋዎች አንዱ የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ ነው፡፡ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን ይገኛል፡፡ ከአዲስ አበባ 178 ኪሎ ሜትር፣ ከጉራጌ ዞን ዋና ከተማ ወልቂጤ ደግሞ 18 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ፓርኩ 360 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ላይ የተንጣለለ ነው፡፡

ተፈጥሯዊ ውበት የተላበሰው ፓርኩ ስያሜውን ያገኘው ከጊቤ ወንዝ እና ከሸለቆው ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የተፈጥሮ ደኖች እና የተለያዩ ዓይነት ዝርያ ያላቸው እጽዋት ማራኪ ገጽታ አጎናጽፈውታል፡፡

ከባህር ጠለል በላይ ከ1 ሺህ 50 እስከ 1 ሺህ 835 ሜትር ድረስ ከፍታ እንዳለው የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ መረጃ ይጠቁማል፡፡

ፓርኩ እንደ ሌሎቹ የሀገራችን ፓርኮች ሁሉ የተፈጥሮ ብዝሃ ሕይወት የሚታይበት ነው፡፡ የቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው ከ12 በላይ ዓመቱን ሙሉ የሚፈስሱ ወንዞች ይገኛሉ፡፡ ወንዞቹም የተለያዩ መጠን ያላቸውን ፏፏቴዎች ይፈጥራሉ፡፡

ለጎብኚዎች ክፍት የሆኑ እንደ ሎቄ፣ ጃቱ እና ሌሎችም ፍል ውሃዎች የፓርኩ ሃብት መሆን ብቻ ሳይሆን የገቢ ምንጭም ጭምራ ናቸው፡፡   

መልክዓ ምድራዊ አቀማመጡም በውስጡ ካሉት ወንዞች፣ እጽዋት እና ሌሎች ዓይንን የሚማርኩ የተፈጥሮ ገጸ-በረከቶች አኳያ እጅግ ማሪኪ ነው፡፡ በእነዚህ ሃብቶች ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡

በርካታ ዝርያዎች ያሏቸው የዱር እንስሳትም መገኛ ነው፡፡ ከ20 በላይ ትላልቅ የተለያዩ ዝርያዎች ያሏቸው የዱር እንስሳት በውስጡ ይኖራሉ፡፡ አንበሳ፣ ጉማሬ፣ አቦ ሸማኔ፣ ጉሬዛ፣ ከርከሮ እና ድኩላ ከብዙ በጥቂቱ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በተጨማም በፓርኩ ዙሪያ በሚፈስሱ እንደ ጊቤ ባሉ ወንዞች አካባቢ አዞዎች እና ጉማሬዎች ይገኛሉ፡፡

ፓርኩ ጥቅጥቅ ባሉ ደኖች፣ ቁጥቋጦዎች እንዲሁም ሜዳማ በሆኑ ሳሮች የተሸፈነ ነው፡፡ ከዚህም መነሻ የተለያዩ ስያሜዎችና ዝርያዎች ያሏቸው እጽዋት በብዛት ይገኛሉ፡፡ አርሙካ፣ ነጭ ዋጮ፣ ቶርቶሊስ፣ ግራር፣ ነጭ ሴባ እና የዕጣን ዛፍ ከእጽዋቶቹ መካከል ይገኙበታል፡፡

ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የፓርኩ ዓመታዊ የዝናብ መጠን በአማካይ ከ900 እስከ 1 ሺህ 400 ሚሊ ሜትር ይደርሳል፡፡ በውስጡ የሚገኙ የአፈር ዓይነቶች አሸዋማ፣ አለቶች፣ ግራጫ፣ ጥቁር አፈር እና ከፍተኛ የሆኑ ሚነራሎች ናቸው፡፡

ታዲያ በዚህ ሁሉ ፀጋዎች የታደለው የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ ከሀገራችን ታላላቅ ፓርኮች አንዱ ነው፡፡ የቱሪዝም ኢኮኖሚን በማሳደግም ረገድ የራሱን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡

የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት በ2017 ዓ.ም ባወጣው መረጃ፣ በዓመቱ 9 ወራት ውስጥ ብቻ ከፓርኩ ከ8 ሚሊየን 100 ሺህ ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል፡፡ ይህ ገቢ የተገኘው ፓርኩን ከጎበኙ 12 ሺህ 540 የሀገር ውስጥና የውጪ ጎብኚዎች ነው፡፡

በአሁኑ ወቅትም መንግስት ከሰጠው ትኩረት አንጻር ገቢው እያደገ መጥቷል፡፡

ለማንኛውም ኢትዮጵያ የጊቤ ሸለቆና መሰል ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ፀጋዎች ባለቤት ናት፡፡ ለብዙ ዘመናት ሃብቱ ቢኖራትም በሚፈለገው መጠን ግን ሳትጠቀምባቸው ኖራለች፡፡

አሁን ግን መንግስት ለእነዚህ ፀጋዎች ተገቢውን ትኩረት እየሰጠ በመሆኑ ሕብረተሰቡም በየአካባቢው የሚገኘውን ሃብት መጠበቅና መንከባከብ አለበት፡፡ በብሔራዊ ቅርስነት የሚታዩትን ደግሞ አቅም በፈቀደ መጠን መጎብኘትና ማበረታታት እንዲሁም ማስተዋወቅ ይገባል እንላለን!

ዘጋቢ፡- ኢያሱ ታዴዎስ