የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓልን ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን በሚያሳይ መልኩ ማክበር እንደሚገባ ተገለፀ
የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓልን ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን በሚያሳይ መልኩ ማክበር እንደሚገባ የቡርጂ ዞን አስተዳደር አስታወቀ፡፡
21ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል በዞኑ በፅዳት ዘመቻ እና በበጎ ተግባራት መከበር ጀምሯል፡፡
በዓሉ ስለሰላም፣ አንድነት እና የአብሮነት እሴቶች ዙሪያ ግንዛቤ በሚፈጥሩ ውይይቶች ትኩረት ሰጥቶ ህዳር 18 ቀን 2019 ዓ.ም “በብዝሃነት የደመቀች፣ በምክክር የጸናች ሥልጡን ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል እንደሚጠቃለል የዞኑ ምክር ቤት ገልጿል።
የቡርጂ ዞን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ተወካይ እና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ታጋሽ ሶሮሞ እንደገለፁት፤ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን አንድነታችንን በሚያሳይ መልኩ በጽዳት ዘመቻ እና በበጎ ተግባራት ላይ በመሳተፍ እስከማጠቃለያ ቀን ድረስ እንደሚከበር ጠቁመዋል፡፡
አያይዘውም በዓሉ በዞኑ ውስጥ በሚገኙ ሦስቱ መዋቅሮች እና ትምህርት ቤቶች እንደሚከበር ገልፀው፤ ስለ ፌዴራሊዝም፣ አብሮነት እና በጋራ የመኖር እሴቶች ዙሪያ ውይይት እንደሚደረግ አመላክተዋል፡፡
በዓሉ ከሁሉም መዋቅሮች የተወጣጡ አካላት በሚያደርጉት ውይይት እና ግንዛቤ መፍጠሪያ መድረክ ቀጥሎ ህዳር 18 ቀን 2019 ዓ.ም በዞን ደረጃ በይፋ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል።
የዚሁ በዓል አካል የሆነው የፅዳት ዘመቻ በሶያማ ከተማ አስተዳደር የተካሄደ ሲሆን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የከተማው ነዋሪዎች እና ከዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡
በፅዳት ዘመቻው ላይ አግኝተን ያነጋገርናቸው የሶያማ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ የሺ ጩማሎ እና በዞኑ ብልፅግና ፓርቲ የሴቶች ክንፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ደስታ አበበ እንዳሉት፤ በዓሉን በማስመልከት በሚከናወኑ መሰል የጽዳት ዘመቻ እና የበጎ ተግባር እንቅስቃሴ ላይ መሳተፍ ከሁላችንም ይጠበቃል ብለዋል፡፡
አክለውም መሰል መልካም ተግባራትን ከመፈፀም ባሻገር አንድነታችንና ሕብረታችንን በማጠናከር ለሰላማችን በጋራ መቆም እና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን በተግባር ማሳየት አለብን ሲሉ አስረድተዋል።
ዘጋቢ፡ አብዶ አየለ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
ወጣቶች ሚዲያ ሲጠቀሙ ከፋፋይ ከሆነ አጀንዳ በመውጣት የማህበረሰቡን አንድነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ሊያተኩሩ ሊገባል
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን መከበሩ ቱባ ባህሎችን ለማስተዋወቅ አስተዋፅኦ አለው – የኮሬ ዞን ምክር ቤት
የመንግስታዊ አገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያ ሪፎርም ትግበራ መጀመሩን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ