በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአሪ ዞን ጤና መምሪያ ከ99 ሺህ በላይ ህጻናትን በተቀናጀ የልጅነት ልምሻ (የፖሊዮ) በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ እንደሆነ አስታወቀ ።
የፖሊዮ በሽታ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ የሚያሳድረውን ጫና ለመቀነስ በክትባት ዘመቻ በየደረጃው ያሉ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ተገልጿል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ በሽታ መከላከል ከፍተኛ ባለሙያና የቢሮ ኃላፊ ተወካይ አቶ ታምራት አሰፋ እንዳስረዱት የፖሊዮ በሽታ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ የሚያሳድረውን ጫና ለመቀነስ የክትባት ዘመቻውን ውጤታማ ለማድረግ በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
የአሪ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ በድሉ በግማስ እንደገለፁት የመጀመሪያ ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከሕዳር 12 እስከ 15 2019 ዓ.ም ለተከታታይ 4 ቀናት የሚካሄድ ሲሆን ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ 99 ሺህ 13 ህጻናት የሚከተቡ መሆናቸውም ገልጸዋል።
የክትባት ዘመቻውን ተደራሽ ከማድረግ ጎን ለጎን ፣ የምግብ እጥረት ያለባቸውን ህፃናትን መለየት፣ የኢቦላ ቫይረስ በሽታን ቤት ለቤት ቅኝትና አስሳ ይደረጋልም ብለዋል።
በማስጀመሪያው መርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የአሪ ዞን ብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊና የዋና አስተዳዳሪ ተወካይ አቶ ገረመው ኃ/ማሪያም በበኩላቸው፤ የነገ ሀገር ተረካቢ ህፃናትን በማስከተብ ከቤተሰብ ጀምሮ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ፖሊዮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ህጻናትን ለዘላቂ የአካል ጉዳትና ሞት የሚዳረግ በሽታ በመሆኑ ትኩረት ሊደረግ ይገባልም ሲሉም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ ተመስገን አሰፋ- ከጂንካ ጣቢያችን።

More Stories
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጠምባሮ ልዩ ወረዳ የመጀመሪያ ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት መሰጠት ተጀመረ
የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በደቡብ ኦሞ ዞን በና ፀማይ ወረዳ በአልዱባ ከተማ ተካሄደ
በተቀናጀ ክትባት ዘመቻ በሀገሪቱ ከ11 ሚሊየን በላይ ህጻናት፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደግሞ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ህጻናት ይከተባሉ – የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት