በተቀናጀ ክትባት ዘመቻ በሀገሪቱ ከ11 ሚሊየን በላይ ህጻናት፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደግሞ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ህጻናት ይከተባሉ – የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
በተቀናጀ ክትባት ዘመቻ በሀገሪቱ ከ11 ሚሊየን በላይ ህጻናት፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደግሞ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ህጻናት እንደሚከተቡ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
ሀገር አቀፍ የተቀናጀ ፖሊዮ ክትባት ማስጀመሪያ መርሀግብር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን ጬንቻ ዙሪያ ወረዳ ተጀምሯል፡፡
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተወካይ አቶ መስፍን ወሰን፣ የፖሊዮ በሽታን ለመከላከል በፌደራልና በክልል መንግሥታት ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከአገራችን ፖሊዮን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት በሁለት ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከህዳር 12 እስከ 15 ቀን 2019 ዓ.ም እንደሚካሄድም ጠቁመዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የጤና ፕሮግራም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ናፍቆት ብርሃኑ፤ የፖሊዮ ቫይረስ የነርቭ ሥርዓትን በማጥቃት የአካል ጉዳትና ሞት ሊያስከትል የሚችል እንዲሁም ፈውስ የሌለው በሽታ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ፖሊዮን ከሀገሪቱ ለማጥፋት በቁርጠኝነት እየሠራች መሆኗን የገለጹት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፣ ይህንን ግብ ለማሳካት ሁሉም የክልሉ ሕፃናት በክትባቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በክልሉ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ፣ በጋሞ ዞን ደግሞ 379 ሺህ ሕፃናትን በዘመቻው ተደራሽ እንደሚደረግ የገለፁት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ምንተስኖት መልካ ናቸው።
በዘመቻው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን በክትባቱ ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር፣ ክትባት ጀምረው ያቋረጡ ሕፃናት ክትባታቸውን እንዲያጠናቅቁ ማድረግ፣ ሕብረተሰቡ ስለ ፖሊዮ ቫይረስ ያለውን ግንዛቤ ማሳደግና የሕፃናትን የሥርዓተ ምግብ ሁኔታ የመለየት ሥራ በተቀናጀ መልኩ እንደሚከናወን አብራርተዋል።
የዓለም አቀፍ የፖሊዮ ማጥፋት ተነሳሽነት የኢትዮጵያ አስተባባሪ ዶ/ር ላቭዴይ ንዋጎ፣ የፌደራልና የክልል ጤና ተቋማት የፖሊዮ ቫይረስን ለማጥፋት እያሳዩ ያሉትን ቁርጠኝነትና ፈጣን ምላሽ አድንቀዋል።
በሀገሪቱ ከ11 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሕፃናት ክትባቱ እንደሚሰጥ የገለጹት አስተባባሪው፣ ክትባቱን ለሁሉም ሕፃናት ተደራሽ በማድረግ የፖሊዮ ቫይረስን ለማጥፋት መንግሥት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሕብረተሰቡና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመላክተዋል።
የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዛኸኝ ጋሞ፤ እንደ ዞን የህፃናትን ጤና ለመጠበቅና ለማስጠበቅ ጠንካራ የፖለቲካ አመራርን ከመስጠት ባሻገር የማህበረሰብ ተሳትፎን ማሳደግ በመቻሉ በዘርፉ እመርታ መታየቱን ተናግረዋል።
በዞኑ መደመር እሳቤና በሀገራዊ የልማት ራዕይው መሰረት የዜጎችን ጤናና ደህንነት ለማስጠበቅ እየተሰራ ይገኛል ያሉት አቶ ገዛኸኝ፤ ይህ ዘመቻም እንዲሳካ ይሰራል ብለዋል።
በመርሀ -ግብሩ የታደሙ የፌደራል፣ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት የጉብኝትና አረንጓዴ አሻራ የማኖር ተግባር አከናውነዋል።
ዘጋቢ፡- ተመኙህ ገረሱ- ከአርባምንጭ ጣቢያችን

More Stories
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጠምባሮ ልዩ ወረዳ የመጀመሪያ ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት መሰጠት ተጀመረ
የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በደቡብ ኦሞ ዞን በና ፀማይ ወረዳ በአልዱባ ከተማ ተካሄደ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአሪ ዞን ጤና መምሪያ ከ99 ሺህ በላይ ህጻናትን በተቀናጀ የልጅነት ልምሻ (የፖሊዮ) በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ እንደሆነ አስታወቀ ።