በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል በትኩረት እየተሠራ ነው – የጌዴኦ ዞን ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ

በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል በትኩረት እየተሠራ ነው – የጌዴኦ ዞን ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ

በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል በትኩረት እየሠራ መሆኑን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጌዴኦ ዞን ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ አስታወቀ።

‎

‎መምሪያው ዓለም አቀፍ የህፃናት እና  የጸረ-ጾታዊ ጥቃት የነጭ ሪቫን ቀንን በዲላ ከተማ አክብሯል።

‎

‎በሴቶች ላይ የሚፈፀመውን የኃይል ጥቃትና ሰብአዊ መብት ጥሰት ለመከላከል በዓለም አቀፍ ደረጃ በህዳር ወር የነጭ ሪቫን ቀን ይከበራል።

‎

‎ዓለም አቀፍ የሕፃናት ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ37ኛ ጊዜ፤ በሀገራችን ደግሞ ለ21ኛ ጊዜ “ትኩረትና እንክብካቤ ለሁሉም ሕጻናት” በሚል እንዲሁም የጸረ-ጾታዊ ጥቃን ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ35ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ21ኛ ጊዜ “ለተጎጂዎች ፍትሕ ለወንጀለኞች ተጠያቂነት፤ ለሴቶችና ታዳጊ ሴቶች ደህንነት”  በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ነው።

‎

‎በመድረኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የጌዴኦ ዞን ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ተወካይ አቶ አለማየሁ አዶላ፤ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል‎ በየዘርፉ ካሉት አደረጃጀቶች፣ ከሃይማኖትና ባህል ተቋማት፣ የፍትህ ተቋማት እንዲሁም በየትምህርት ቤቱ ከተቋቋሙ ክበባት ጋር የቅድመ መከላከል ሥራ ላይ በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

‎

‎በሴቶችና ሕፃናት ላይ የአካልና የስነልቦና ጥቃት ሲፈፀም ከህግ ባለሙያዎች ጋር በመሆን ፍትህ እንዲያገኙ እንደሚሰሩ ጠቅሰው፤ ህጉ በሚደነግገው መሰረት በአጥፊዎች ላይ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ማድረጋቸውንም አቶ አለማየሁ አብራርተዋል።

‎

‎በመድረኩ ንግግር ያደረጉት  የጌዴኦ ዞን አስተዳዳር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ  አቶ ዳንኤል ስዩም በበኩላቸው፤ በሴቶችና ህጻናት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሰጥቶ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

‎

‎አክለውም ሴቶችና ሕፃናት ለጥቃት ተጋላጭ ስለሆኑ ይህንን ለመከላከል ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

‎

‎የበዓሉ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ በህጻናትና ሴቶች ላይ ጥቃት እንዳይደርስ መጠበቅ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን አንስተው፤ በተለያዩ ጊዜያት የሚፈፀሙ የህግ ጥሰቶችን ለመከላከል የሚመለከታቸው አካላት ከሕብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጠይቀዋል።

‎

‎በበዓሉ ላይ የጌዴኦ ዞን የህጻናት ፓርላማ ተወካዮች፣ የዞን፣ የወረዳና ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች፣  የህጻናት መብት ማስጠበቂያ ቡድን መሪዎች ተገኝቷል።

‎

‎‎ዘጋቢ፡ ውብሸት ኃ/ማርያም – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን