የተስፋ ቃል

የተስፋ ቃል

ችግኝ ብቻ አይደለም አንቺን ማስታወሻ ቃሌንም ተክላለሁ፣
በለም አፈርሽ ላይ በአረንጓዴ ቀለም ህይወት ከትባለሁ፡፡

ሊጠፋ የማይችል ብሩሁ ተስፋዬን ምድርሽ ላይ አስፍሬ፣
ለም መስክን ለማውረስ በዛሬው ውሎዬ ከነግ ተቃጥሬ፣
በተስፋ ጉልላት ከመጠሪያሽ ማማ አድማስ ተሻግሬ፣
ከተፈጥሮሽ ማዕድ በመቋደስ ጉጉት ከትውልድ አብሬ፣
አኖራለሁ ስሜን ሊፋቅ በማይችለው ጥቁሩ ሸራሽ ላይ፣
የመወደዴ ጥጉ ንግርቴን ተሻግሮ በተግባር እንዲታይ፡፡

እመኚኝ እማማ መውደዴን ለመግለጽ ቃላትን ባልሰድር፣
ስ‘ላንቺ እያዜምኩ በልዩ ችሎታ ክራር ባልደረድር፣
የሰራሁት ባይኖር በዓለም አደባባይ ስምሽን የሚያስጠራ፣
ባላውለበልበው ባንዲራሽን ይዤ ባልወጣ ተራራ፡፡

እህ ብለሽ ስሚኝ ስላለፈው ሳይሆን ላውጋሽ ስ‘ላሁኔ፣
ተስፋን በመትከል ጽንፍ በሸከፍኩት ወኔ፣
እንደ አክሱም የሚቆም ዘመን የማይሽረው፣
እንደ ላሊበላ እንደ ፋሲል ግንብሽ እልፍ የሚጎበኘው፣
እንደ ጥያ ትክል ድንጋይ ታሪክን ነጋሪ፣
ነበርን አስታዋሽ ያለፈን ዘካሪ፣
እንደ አባጅፋር ውብ ተወዳጅ ቤትሽ፣
የእጅ ጥበብ ምርኮ እንደ ኮንሶ እርከንሽ፣
ተቀማጭ የሚሆን የሚችል ሊያስጠራኝ፣
ከማይፈርስ ቃሌ ጋር እተክላለሁ ችግኝ፡፡

እናማ እማማዬ!
ከባንዲራሽ አናት በአሃዱ ቀለም፣
ትርጉም በሚሰጠው በቃላት ሲሰየም፣
ደምቆ በሚታየው በዛ ውበት አዘል፣
ከማርያም መቀነት ከቀለማት መሀል፣
በአረንጓዴ ቀለም በጥቁር ሸራሽ ላይ፣
ያርፋል አሻራዬ ለትውልድ የሚቆይ፡፡

ከዚያ ወዲያ አለሜ፣
በጥቁሩ ሸራሽ ላይ ሲከትም ቀለሜ፣
በምተክለው ችግኝ ይሰየማል ስሜ፡፡
ግና….
የምተክለው ችግኝ እልፍ አዕላፍ ሆኖ ከየትም ቢበቅልም፣
ባብቃዩ በእኔ እጂ በሌላ አይጠራም፡፡

ስለዚህ አበባዬ እናት ሀገር ቤቴ!
ልክ እንደ ችግኜ የትም ተተክዬ ከየትም ብበቅልም፣
ካ‘ንድ አንቺ በስተቀር ከጦቢያዬ ሌላ መጠሪያ የለኝም፡፡

ለምልሚልኝ እቴ አንቺን ለማለምለም ምክንያት አያሻኝም፣
መጠሪያ ከሆንሽን ስምሽ ከተቸረኝ ሌላን አልፈልግም፡፡
እና…. እንደነገርኩሽ!
ከቃሌ ጋር እንጂ ችግኜን አልተክልም ከቃሌ ለይቼ፣
ተስፋን እየተከልኩ በተስፋ እንድጓዝ ተስፋዬን አንግቼ፡፡

ለምን?… ያልሽኝ እንደው
ሳት እንዳልል በጎዳናው ተስፋ እምነቴን ጥዬ፣
አብሬ ልትከለው በቅሎ እንዲታይ እንዲሆን እዳዬ፡፡

ገጣሚ፡- ሸዊት ሂርጶ