ኢትዮጵያ ወገቧን ጠበቅ አድርጋ ልታሰናዳ የተዘጋጀችው ኮፕ 32 ጉባኤ

ኢትዮጵያ ወገቧን ጠበቅ አድርጋ ልታሰናዳ የተዘጋጀችው ኮፕ 32 ጉባኤ

ልክ የዛሬ 1 ዓመት የኋሊት ትናንትናን ስንቃኝ ኮፕ 30 ጉባኤን እናገኛለን፡፡ ከአውሮፓዊያኑ ሕዳር 10 እስከ 21 ቀን 2025 በብራዚሏ ቤሌም ከተማ የተዘጋጀው 30ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ እንደ ሌሎቹ ጊዜያቶች ሁሉ በስኬት የተጠናቀቀ ነበር፡፡

የብራዚል መለያ በሆነው አማዞን ጫካ ክልል አካል በሆነችው ቤሌም ከተማ ጉባኤው ሲካሄድ፣ ከቱርክዬው ጉባኤ በመቀጠል የኮፕ 32 2027 አዘጋጅ ሀገር መመረጧ አልቀረም፡፡ ታዲያ ምርጫው ሲካሄድ ዕጣው የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ታትራ እየሰራች የምትገኘው ኢትዮጵያ ላይ ወደቀ፡፡

የኢትዮጵያን መመረጥ ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የኮፕ 32 ፕሬዝደንት ሆነው ተመርጠዋል፡፡

ኢትዮጵያ ይህንን ዕድል ያገኘችበት የራሱ አካሄድ ነበር፡፡ የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (cop) በተለያዩ የዓለማችን ከተሞች በየዙሩ በየዓመቱ ይካሄዳል፡፡ በአውሮፓዊያኑ 2027 ጉባኤውን የማዘጋጀት ተራው ለአፍሪካ ደርሶ ነበር፡፡

ታዲያ ይህን ተከትሎ ከኢትዮጵያ ቀድማ ናይጄሪያ ነበረች የአዘጋጅነት ጥያቄውን ያቀረበችው፡፡ ናይጄሪያ በመጋቢት ወር 2025 ጉባኤውን ለማዘጋጀት ፍላጎቷን አሳውቃ ነበር፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ በመስከረም ወር 2025 የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን አዲስ አበባ ላይ አዘጋጅታ ኮፕ 32 ጉባኤን ማዘጋጀት እንደምትፈልግ በይፋ ጥያቄዋን አቀረበች፡፡

ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት ዋና መቀመጫ መሆኗ፣ ብሎም የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤንና ሌሎች ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በስኬት ማዘጋጀቷ ናይጄሪያን ጨምሮ የአፍሪካ ተደራዳሪዎች ቡድንን አሳምኖ በመጨረሻም ኢትዮጵያ መመረጥ ችላለች፡፡

ከዚህ ጊዜ በኋላ የኢትዮጵያ ትኩረት የጉባኤው ዝግጅት ላይ ሆኗል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቱርክዬ አንታሊያ እየተካሄደ በሚገኘው ኮፕ 31 ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ጉባኤውን ለማዘጋጀት ስላላት ቁርጠኝነት እና ቁልፍ የትኩረት አቅጣጫዎች ይፋ አድርገዋል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የአየር ንብረት ለውጥ ማስጠንቀቂያዎች ሲወጡ ፈጣን ምላሽ መስጠት ላይ ትኩረት እንደሚደረግ አረጋግጠዋል፡፡ የአየር ንብረት ፋይናንስን በተመለከተ ቃል ከመግባት ባለፈ በፍጥነት ተለቅቆ ለአደጋ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ ማህበረሰቦች ቀድሞ እንዲደርስ ጥረት እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም ኢትዮጵያ ከኮፕ 31 አዘጋጆች ጋር በቅርበት እንደምትሰራ ከማረጋገጣቸውም በላይ የዓለም መሪዎችንና ተሳታፊዎችን ለጉባኤው ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

የኮፕ 32 ጉባኤ በመጪው ዓመት በአዲስ አበባ ከአውሮፓዊያኑ ሕዳር 8 እስከ 19 ቀን 2027 ድረስ ይካሄዳል፡፡ ዝግጅቱን በበላይነት የሚመራ ብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራዎች እየተገመገሙ መሆናቸውን መንግስት አስታውቋል፡፡

ዘጋቢ፡- ኢያሱ ታዴዎስ