የዞኑን ሰላምና ጸጥታ በማስጠበቅ የልማትና ዕድገት ሥራዎችን ለማረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻዎች ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ
የዞኑን ሰላምና ጸጥታ በማስጠበቅ የልማትና ዕድገት ሥራዎችን ለማረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻዎች ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የጌዴኦ ዞን አስተዳደር አስታወቀ፡፡
በጌዴኦ ዞን ሠላምና ጸጥታ መምሪያ “ለሠላም ሠላም መሆን” በሚል መሪ ቃል የ2019 ዓ.ም የመጀመሪያ ዙር የጸጥታ ምክር ቤት ጉባዔ የውይይት መድረክ በይርጋጨፌ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ሠላም የልማት፣ የዕድገትና የሰው ልጅ ሁሉ የህልውና መሠረት በመሆኑ ሁሉም ሰላምን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በተግባር መደገፍ ይጠበቅበታል ተብሏል።
የይርጋጨፌ ከተማ ከንቲባ አቶ መንግሥቱ ተክሌ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላለፉትበት ወቅት በይርጋጨፌ ከተማ ሰላምን በማስጠበቅ ረገድ በኮማንድፖስት የሚመራ ጠንካራ አደረጃጀት መኖሩን ጠቁመው፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በመረባረብ ጥሩ ውጤት ለማምጣት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው የጌዴኦ ዞን የፀጥታ ምክር ቤት ጉባኤ በይርጋጨፌ ከተማ በመካሄዱ መደሰታቸውን የገለጹት ከንቲባው፤ ይህ የተረጋጋ ሠላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የምክር ቤቱ አባላት በትኩረት መስራት እንደሚገባቸው አንስተዋል።
የጌዴኦ ዞን ሠላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሽብሩ ሚጁ በበኩላቸው፤ የሰላም ጉዳይ በመንግሥት የጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች ብቻ የሚረጋገጥ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ ያለውን ሰላም በይበልጥ ለማስቀጠል ሁሉም አካላት በቅንጅት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
አስተማማኝ ሰላም እንዲፈጠር በተለያዩ ጊዜያት ከአከባቢ የጸጥታ አካላት ጋር በተደረጉ ውይይቶች በዞኑ ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን አንስተው፤ አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ኮንትሮባንድና የቡና ዝውውር ወንጀሎችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስገንዝበዋል።
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር መስፍን ደምሴ ባደረጉት ንግግር፤ የጌዴኦ ሕዝብ ወንጀልን ለመከላከልና አካባቢውን መጠበቅ ያስቻሉ ባሕላዊ የሰላም እሴቶች እንዳሉት ገልፀው፤ በመልካም ስነ-ምግባር የታነጹ ዜጎችን ለማፍራት የሰላም አደረጃጀቶች አጋዥ ኃይል በመሆናቸው በሁሉም ተቋማት የሰላም ኮሚቴ አደረጃጀቶችን የማጠናከርና የመደገፍ ሥራዎች በትኩረት ሊሠራባቸው ይገባል ብለዋል።
አያይዘውም ሠላምና ጸጥታ አስከባሪዎች ሰላምና ጸጥታን ከመጠበቅ አንጻር ቀዳሚ ሚናቸውን የሚወጡ ቢሆንም ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል የራሱን አከባቢ ከመጠበቅ አንጻር የሮንድ ጥበቃ ሥራዎች ላይ የተጠናከረ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በመድረኩ የከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መንግሥቱ ተክሌን ጨምሮ አጠቃላይ የዞኑ የጸጥታ አስባሪዎች፣ የየወረዳዎቹ አመራሮች፣ የባህል ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ተሳትፈውበታል።
ዘጋቢ፡ እስራኤል ብርሃኑ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
የሃይማኖት ተቋማት ዜጎች በራሳቸው ጥረት ኑሯቸውን የማሻሻል እና ሌሎችን የማገልገል የሞራል ግዴታን በማስተማር ረገድ ሚናቸው የጎላ መሆኑ ተገለፀ
ጋና ለዓለም ያበሰረችው ምንድነው?
የጥቁር አዝሙድ ምርት ለአርሶአደሩ ከምግብ ፍጆታ ባሻገር የገቢ ምንጭ የመሆን አቅም እንዳለዉ ተገለፀ