የጥቁር አዝሙድ ምርት ለአርሶአደሩ ከምግብ ፍጆታ ባሻገር የገቢ ምንጭ የመሆን አቅም እንዳለዉ ተገለፀ
የጥቁር አዝሙድ ምርት ለአርሶአደሩ ከምግብ ፍጆታ ባሻገር የገቢ ምንጭ የመሆን አቅም እንዳለዉ በቀቤና ልዩ ወረዳ የሚገኙ አምራች አርሶ አደሮች ገለጹ።
አርሶአደሩ የተለመዱ ሰብሎች ላይ ጥገኛ ከመሆን ተላቆ አዳዲስ ሰብሎችን በማስፋት ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ የልዩ ወረዳው ግብርና ጽ/ቤቱ እየሰራ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።
በግብርናዉ ዘርፍ አዳዲስ ሰብሎችን በመለየትና በማላመድ አርሶአደሩን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ እና የገቢ አማራጩን ለማስፋት እየተሰራ ይገኛል።
በቀቤና ልዩ ወረዳ የሪሙጋ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶአደር በድሩ ኑሮ እና አንዋር ጀማል በቀበሌያቸው ከዚህ ቀደም በቆሎን ጨምሮ በተለያዩ ሰብሎች ማሳቸዉን ይሸፍኑ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በዘንድሮ መኸር እርሻ ግን በአከባቢው በስፋት ያልተለመደውን የጥቁር አዝሙድ ሰብል በሁለት ሄክታር መሬት ላይ መዝራታቸውን ገልፀዋል።
አርሶአደሮቹ በዘንድሮ አመት ካለሙት የጥቁር አዝሙድ ሰብል በሄክታር ከአስር ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ብለዉ እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
የጥቅር አዝሙድ ሰብል በምግብ ዝግጅት፣ በቅመምነትና በተለያዩ የምግብ ማቀነባበሪያ ዘርፎች ጥቅም እንደሚሰጥ በመጥቀስ፤ ምርቱ ለአርሶአደሩ ከምግብ ፍጆታ ባሻገር የገቢ ምንጭ የመሆን አቅም እንዳለዉም ጠቁመዋል።
በቀቤና ልዩ ወረዳ የሪሙጋ ቀበሌ የግብርና ባለሙያ የሆኑት አቶ ሙስጠፋ ጀማል በበኩላቸው፤ አርሶአደሩ በተለያዩ የግብርና ዘርፎች ዉጤታማ እንዲሆን ሙያዊ ድጋፎችን እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት የአርሶአደሩ ማሳ በቋሚና በጥራጥሬ ሰብሎች ይሸፈን እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ እንደ ጥቅር አዝሙድ፣ ተልባ በመሳሰሉ ቅመማ ቅመሞች በመኸርና በበጋ መስኖ እየለማ በመሆኑ የአርሶአደሩ ተጠቃሚነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።
የቀቤና ልዩ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብድልሽኩር ደሊል በግብርናው ዘርፍ የአርሶአደሩን ኑሮ ለማሻሻልና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ሁሉ አቀፍ የተቀናጀ የግብርና ስራ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በልዩ ወረዳዉ አዲስ ኢንሼቲቭ የሆኑት የቅመማ ቅመም ሰብሎች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በዘንድሮ ምርት ዘመን 700 ሄክታር በርበሬ፣ 350 ሄክታር ጥቁር አዝሙድ እና 150 ሄክታር ማሳ በቺያስዴ ሰብል ተሸፍኖ ምርት እየተሰበሰበ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አርሶአደሩ የተለመዱ ሰብሎች ላይ ብቻ ጥገኛ ከመሆን ተላቆ አዳዲስ ሰብሎችን በማስፋት ተጠቃሚነቱን እንዲያረጋግጥ ጽሕፈት ቤቱ እየሰራ እንደሚገኝ ኃላፊዉ አቶ አብድልሽኩር ገልፀዋል።
ዘጋቢ፡ ሪያድ ሙህዲን – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
አርሰናል ከዴቪድ ራያ ጋር አዲስ ኮንትራት ለመፈራረም ተስማማ
ለክትባት ዘመቻው ስኬት ሚዲያዎችና ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ
ጥቂት ስለድንጋይ ከሰል ምርት