ሙስሊሙን ወጣት በወንድማማችነት መንፈስ በማሰባሰብ በእስላማዊ እውቀትም ሆነ በኢኮኖሚው መስክ ውጤታማ እንዲሆን ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሙስሊም ወጣቶች ካውንስል አስታወቀ

ሙስሊሙን ወጣት በወንድማማችነት መንፈስ በማሰባሰብ በእስላማዊ እውቀትም ሆነ በኢኮኖሚው መስክ ውጤታማ እንዲሆን ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሙስሊም ወጣቶች ካውንስል አስታወቀ

ይህ የተገለጸው የኣሪና ደቡብ ኦሞ ዞኖችና የጂንካ ከተማ አስተዳደር የሙስሊም ወጣቶች ካውንስሎች ምስረታ በተካሄደበት ወቅት ነው።

በዚሁ ወቅት ንግግር ያደረጉት የኣሪ ዞን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሸህ ጀማል መሐመድ፤ የሙስሊም ወጣቶች በአባቶቻችን ዘመን ከአደረጃጀት ጋር የተያያዙ ችግሮች መኖራቸውን ጠቅሰው በመደመር መንግስት አደረጃጀት መመስረቱ የሚያስመሰግን መሆኑን ገልጸዋል።

አደረጃጀቱ አጎራባች ዞንን ያካተተ በመሆኑ ለወጣቶች ልምድ ልውውጥ ምቹ ሆኔታ ይፈጥራልም ብለዋል።

የክልሉ ሙስሊም ወጣቶ ካውንስል ዋና አሚርና ሰብሳቢ ወጣት ሉባ ወልዴ፤ ካውንስሉ የአባቶቻችን ትግል ውጤት መሆኑን ጠቅሰው አደረጃጀቱን በመጠቀም ወጣቱ ራሱን ጠቅሞ ሌሎችንም ሊጠቅምበት ይጠባል ብለዋል።

የኣሪና ደቡብ ኦሞ ዞን የሙስሊም ወጣቶች ካውንስል መመስረት ወንድማማችነትን ማጽናትን ወጣቱ ከእስላማዊ ተልዕኮ ባሻገር በእውቀትም በኢኮኖሚያዊ ለውጥም ማምጣት ሌላኛው ግብ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም የሙስሊም ወጣቶችን የልማት ተሳታፊነት እንደሚያሳድግ በመረዳት ለክልሉ ሰላም ዘብ ሊሆኑ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የሀገሪቱ ብዝሃነት ሀይማኖት አንዱ መገለጫ የሆነው እስልምናን ከልማዳዊ አሰራር ለማላቀቅ የተጀመሩ ጥረቶችን ያደነቁት ደግሞ በመድረኩ የተገኙት የኣሪ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደመላሽ አቦነህ ናቸው።

የካውንስሎቹ ምስረታ የመደመር መንግስት የአመራር ሪፎርም በተደረገ ማግስት መሆኑ ለየት ያደርገዋል ብለዋል ኃላፊው።

በወጣቱ ውስጥ የሚስተዋሉ የአመለካከት ዝንፈቶችን የማረምና የተሻለ ሥነ ምግባር ያለው ትውልድ በመገንባት አርአያ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ በኃይሉ ወንድሙ እስልምና በሀገረ መንግስት ግንባታ የራሱ የሆነ አበርክቶ ያለው ቀደምት እምነት መሆኑን ተናግረዋል።

ሙስሊሙ ወጣት በመንፈሳዊ እውቀትም ሆነ በሥነ ምግባር እዲታነጽ በማድረግ ረገድ አደረጃጀቱ ወሳኝ ሚና ሊኖረው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ለአደረጃጀቱ ውጤታማነትም በከተማ አስተዳደሩ በኩል አስፈላጊ ድጋፎች እንደሚደረጉም አረጋግጠዋል።

በመድረኩ ለካውንስሎቹ በስራ አስፈጻሚነት የተመረጡ ወጣቶችም ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።

የሁለቱ ዞኖች እስልምና ጉዳዮች ሞክር ቤት ሰብሳቢዎች የሥራ አስፈጻሚ አባላትም የተሰጣቸውን የህዝብ አደራ በተጠያቂነት መንፈስ እንዲወጡ አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡ ወንድሜነህ አድማሱ – ከጂንካ ጣቢያችን