የFOLUR ETHIOPIA ፕሮጀክት የሁለት ዓመት ተኩል አፈጻጸም በአገር አቀፍና ዓለም አቀፍ አማካሪዎች እየተገመገመ ነው
የአርሶ አደሩን የኑሮ ሁኔታ በዘላቂነት ለመለወጥ፣ የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የተፈጥሮ ሀብትን ለመጠበቅና የደን መመናመንን ለመከላከል ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ የሚገኘው የFOLUR ETHIOPIA ፕሮጀክት የሁለት ዓመት ተኩል የትግበራ አፈጻጸም በአገር አቀፍና ዓለም አቀፍ አማካሪዎች እየተገመገመ መሆኑ ተገለጸ።
ፕሮጀክቱ ከዓለም አቀፉ የአካባቢ ፋሲሊቲ (GEF) የገንዘብ ድጋፍና ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) የቴክኒክ ድጋፍ በማግኘት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጌዴኦ ዞን በወናጎ፣ ይርጋጨፌና ኮቾሬ ወረዳዎች እየተተገበረ የሚገኝ መሆኑ ተጠቁሟል።
የFOLUR ETHIOPIA ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አለምበጁ ክፍሌ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ የተቀናጀ የመሬት አያያዝን በማስፋፋት፣ የቡና ዝርያዎችን ዕሴት በመጨመር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ የምግብ ሥርዓትን በማጠናከር፣ የተፈጥሮ ደኖችና ሌሎች ሀብቶች እንዲጠበቁና እንዲያገግሙ ከማድረግ ባለፈ የእውቀት ሽግግርን ማሳለጥ ዋና ዓላማዎቹ ናቸው።
በሦስቱም ወረዳዎች በእያንዳንዳቸው በአምስት ቀበሌዎች፣ በድምሩ በ15 ቀበሌዎች የመሬት አጠቃቀም ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መግባቱንም አስተባባሪው ገልጸዋል።
ያረጁና ምርት መስጠት ያቆሙ የቡና ሰብሎችን በመተካትና በጉንደላ የማደስ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አለምበጁ፣ እስካሁን በ633 ሄክታር መሬት ላይ የቡና ማደስ ሥራ መከናወኑን አስረድተዋል።
ከዚህም ውስጥ በ461 ሄክታር መሬት ላይ ያረጁትን የቡና ሰብሎች በአዳዲስ የቡና ዝርያዎች የመተካት ሥራ ሲከናወን፣ በቀሪው 172 ሄክታር መሬት ላይ ደግሞ በጉንደላ የማደስ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የደን መጨፍጨፍን ለመከላከልና የማገዶ ፍጆታን ለመቀነስ ለ4 ሺህ 879 እማወራዎች ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን የማሰራጨትና ስልጠና የመስጠት ሥራ መከናወኑ ተመላክቷል።
ፕሮጀክቱ በሁለት ዓመት ተኩል የትግበራ ቆይታው የታለመለትን ዓላማ ማሳካት መቻሉንና የተከናወኑ ሥራዎች ያላቸውን ውጤት ለመገምገም ከአገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ የተውጣጡ አማካሪዎች በተለያዩ አካባቢዎች የመስክ ጉብኝት እያደረጉ መሆኑን አቶ አለምበጁ ጠቁመው፤ የግምገማው ውጤትም ለፕላንና ልማት ሚኒስቴርና ለUNDP እንደሚቀርብ ተናግረዋል።
ከገምጋሚዎቹ መካከል አቶ ይልቃል አዲሱ በበኩላቸው፣ የFOLUR ETHIOPIA ፕሮጀክት የተፈጥሮ ደኖች በመመናመናቸው ምክንያት የሚከሰቱ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም፣ የደን ሀብትን ለመጠበቅና ዘላቂ የቡና ምርትን ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ በአራት ክልሎች በሚገኙ 22 ወረዳዎች የሚከናወኑ የፕሮጀክቱን ተግባራት እየገመገሙ መሆኑን የገለጹት አቶ ይልቃል፣ በሲዳማ ክልል የመስክ ጉብኝታቸውን አጠናቀው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጉብኝት እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
በጉብኝታቸውም ህብረተሰቡ በጋራ በኩታ ገጠም የሚያከናውነው የግብርና ሥራ፣ ከ50 በላይ አርሶ አደሮች በትብብር መሥራታቸው፣ ለወጣቶችና ለሴቶች የተሠሩ ሥራዎች እንዲሁም በመሬት ላይ ያዩት ተጨባጭ ውጤት እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።
የኮቾሬ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘነበ አብርሃም በበኩላቸው፣ በአገር ደረጃ የሚተገበሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ድክመትና ጥንካሬ በተገቢው ሁኔታ ተገምግመው መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች ካልታወቁ የታለመላቸውን ውጤት ማምጣት እንደሚቸገሩ ገልጸዋል።
የFOLUR ETHIOPIA ፕሮጀክት ጠንካራ ጎኖችና መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች በአገር ውስጥና በውጭ ገምጋሚዎች መገምገማቸው ለፕሮጀክቱ የበለጠ ውጤታማነት እንደሚያግዝ አስረድተዋል።
በወረዳው በፕሮጀክቱ የተከናወኑ ልማቶችንና በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ዕድሜ ላይ የደረሱ ሰብሎችን በመመልከት የአርሶ አደሩ ግንዛቤ እየሰፋ መምጣቱን የጠቆሙት አቶ ዘነበ፣ የተገኘውን ልምድና ውጤት ወደ ሌሎች አካባቢዎችም ለማስፋፋት እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በ27.5 ሄክታር መሬት ላይ 49 አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም ያከናወኑት የግብርና ልማት ቀደም ሲል ያረጀ ቡና ብቻ የነበረበትን መሬት ወደ ምርታማ የልማት ሥፍራ መቀየሩን የኩታ ገጠም ተወካዩ ገልጸው፣ ለፕሮጀክቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በአጠቃላይ የFOLUR ETHIOPIA ፕሮጀክት በቡና ልማት፣ በተቀናጀ የመሬት አጠቃቀም፣ በደን ጥበቃና በማህበረሰብ ተሳትፎ ዙሪያ ያከናወናቸውን ተግባራት በመገምገም የተገኙ ጥንካሬዎችን ለማስቀጠልና መሻሻል ያለባቸውን ጉዳዮች ለማረም የሚያስችል አቅጣጫ እንደሚያመላክት ይጠበቃል።
ዘጋቢ፡ ውብሸት ካሳሁን – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
የFOLUR ETHIOPIA ፕሮጀክት የሁለት ዓመት ተኩል አፈጻጸም በአገር አቀፍና ዓለም አቀፍ አማካሪዎች እየተገመገመ ነው

More Stories
የህዝቦችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እና የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን ወሳኝ ነው – አቶ ኡስማን ሱሩር
የወልቂጤ ግብርና ምርምር ማዕከል አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በማመንጨት በማባዛትና በማስተዋወቅ የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት እንዲሻሻል ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ገለፀ
ብቁ፣ ተወዳዳሪና ውጤታማ ትውልድ ለማፍራት በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ ተገለፀ