የኤዝሪ ኮንሳ እና ጋብሬል ማጋሌሽ ድንቅ ጥምረት በአርሰናል

የኤዝሪ ኮንሳ እና ጋብሬል ማጋሌሽ ድንቅ ጥምረት በአርሰናል

የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል ባለፈው ሐምሌ ወር ላይ ቁልፍ የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ ዊልያም ሳሊባ በከባድ የጀርባ ጉዳት ምክንያት ለረጅም ጊዜ ከሜዳ እንደሚርቅ ባስታወቀ ጊዜ ደጋፊዎች ከፍተኛ ስጋት አድሮባቸው ነበር።

ፈረንሳዊው ተከላካይ ሳሊባ ከጋብሬል ማጋሌሽ ጋር በመሆን ጠንካራ የተከላካይ ጥምረት በመፍጠር አርሰናል ባለፈው የውድድር ዘመን 27 የሊግ ጎሎችን ብቻ አስተናግዶ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ እንዲያነሳ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጎ ነበር።

አዲሱ የውድድር ዘመን ተጀምሮ ስምንት ጨዋታዎች ከተካሄዱ በኋላ ሳሊባ እስካሁን ወደ ሜዳ ባይመለስም፣ የሚኬል አርቴታ ቡድን በፕሪሚየር ሊጉ ዝቅተኛ ጎል የተቆጠረበት ክለብ በመሆን በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ እኩል ነጥብ ይዞ ይገኛል።

ለዚህ ውጤታማነት ደግሞ በነሐሴ ወር ከአስቶንቪላ በ55 ሚሊዮን ፓውንድ አርሰናልን የተቀላቀለው የ29 ዓመቱ ኤዝሪ ኮንሳ ያሳየው አስደናቂ ብቃት ተጠቃሽ ነው።

ኮንሳ አርሰናልን ከመቀላቀሉ በፊት በክለቡ ደጋፊዎች እና እግር ኳስ ተንታኞች ዘንድ በርካታ ጥያቄዎች ተነስተው ነበር።

ክርስቲያን ሞስኬራ ጨምሮ በስብስቡ ውስጥ ሰባት ተከላካይ እያለ ለምን ይህን ያህል ከፍተኛ ገንዘብ ወጣ? ከፊት ተጫዋች ይልቅ ተከላካይ ማስፈረም አስፈላጊ ነበር? የሚሉ።

ነገር ግን አሁን ላይ ክርክሩ ኮንሳ እና ጋብሬል ማጋሌሽ በፕሪሚየር ሊጉ ብቻ ሳይሆን በዓለም እግር ኳስ ውስጥ ምርጡ የተከላካይ ጥምረት ናቸው ወይ? ወደሚል ተቀይሯል።

ኮንሳ አስቶንቪላን በ2019 ከተቀላቀለ በኋላ 286 ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን፣ ባለፈው ግንቦት ወር ላይ የቀድሞ ክለቡ የዩሮፓ ሊግ ዋንጫን እንዲያነሳ ረድቷል።

በተጨማሪም ለእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ቋሚ ተሰላፊ በመሆን በ2026ቱ ዓለም ዋንጫ ላይ ከተካሄዱት ስምንት ጨዋታዎች በሰባቱ ላይ በቋሚነት ተሰልፏል።

የመድፈኞቹ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታም የኮንሳን በፍጥነት ከቡድኑ ጋር መላመድ “አስደናቂ” ሲሉ አሞካሽተውታል።

አርሰናል በዚህ ዓመት ያስመዘገባቸው አኃዛዊ መረጃዎችም ይህንን ያረጋግጣሉ።

ኮንሳ ባለፈው የውድድር ዘመን በፕሪሚየር ሊጉ ከፍተኛ የኳስ ማቀበል ስኬት የነበረው ተጫዋች ሲሆን፣ ዘንድሮም ካደረጋቸው 324 ኳሶች 96% ያህሉን በስኬት በማቀበል በሰንጠረዡ አናት ላይ ይገኛል።

አርሰናል በሊጉ ካደረጋቸው 8 ጨዋታዎች በ5ቱ ላይ ግብ አላስተናገደም።

ኮንሳ እና ጋብሬል በአንድ ላይ ከጀመሯቸው 9 ጨዋታዎች መካከል 7ቱን ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን፣ በ5ቱ መረባቸውን ሳያስደፍሩ ከመውጣታቸው ባሻገር 2 ግቦችን በጋራ ማስቆጠር ችለዋል።

ባለፈው ቅዳሜ አርሰናል ኤቨርተንን 2ለ0 ባሸነፈበት ጨዋታ ኮንሳ የመጀመሪያውን ግብ ያስቆጠረ ሲሆን፣ ጋብሬልም በተመሳሳይ ግብ በማስቆጠሩ ከ2024 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለቱ የአርሰናል የመሐል ተከላካዮች በአንድ ጨዋታ ግብ ማስቆጠር ችለዋል።

በተጨማሪም በቻምፒየንስ ሊጉ አርሰናል ባደረጋቸው 3 ጨዋታዎች በሙሉ ሁለቱ በቋሚነት ተሰልፈው አርሰናል እስካሁን ሽንፈትን አላስተናገደም።

የቀድሞው የአርሰናል ተከላካይ ማርቲን ኪዮን ስለ ኮንሳ ሲናገር”ሳሊባ እና ጋብሪኤል በባሎንዶር እጩነት ውስጥ የነበሩ የዓለም ምርጥ ተከላካዮች ናቸው። ኮንሳ ግን አብሮዋቸው ከሚጫወቱት ተጫዋቾች ጥላ ስር ሳይወድቅ በራሱ ትልቅ ብቃት ማሳየት ችሏል” ብሏል።

አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ በበኩላቸው ሳሊባ አሁንም በሜዳ ላይ የግል ልምምድ ማድረግ ቢጀምርም፣ ኮንሳ እያሳየ በሚያስመለክተው ብቃት ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

“ዊሊያም ሳሊባ ቶሎ እንዲመለስ እንፈልጋለን” ያሉት እፔናዊው አሰልጣኝ “ነገር ግን ኮንሳ ያለ ምንም ቅድመ-ውድድር ዘመን ዝግጅት ወደ አርሰናል መጥቶ፣ በዚህ ደረጃ መጫወቱና ከጋብሪኤል ጋር በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህንን ያህል ጠንካራ ጥምረት መፍጠሩ በጣም ከባድ ስራ ነው፤ እርሱን በማግኘታችን እድለኞች ነን” ብለዋል።

ሳሊባ በአሁኑ ወቅት በሳር ሜዳ ላይ የግል ልምምዶችን ማድረግ የጀመረ ቢሆንም፣ ወደ ጨዋታ የሚመለስበት ትክክለኛ ቀን አልተወሰነም። አርቴታ ሳሊባ በፍጥነት እንዲመለስ ፍላጎት እንዳላቸው ቢገልጹም፣ የኮንሳ እና የጋብሬል ጠንካራ ጥምረት ቡድኑ ያለ ሳሊባም ቢሆን በከፍተኛ ብቃት እንዲቀጥል አስችሎታል።

ሳሊባ ሙሉ በሙሉ አግግሞ ሲመለስ ለኮንሳ አዲስ ፈተና ሊሆን ይችላል። ሆኖም ግን ኮንሳ በመሐል ተከላካይነት ብቻ ሳይሆን በቀኝ የመስመር ተከላካይነት መጫወት መቻሉ በቋሚ ተሰላፊነት ውስጥ የመካተት እድሉን ሰፊ ያደርገዋል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ