የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስቀድሙ እና የሕዝብን አንድነት የሚያጠናክሩ ሊሆኑ ይገባል – ዶክተር ለገሰ ቱሉ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 04/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስቀድሙ እና የሕዝብን አንድነት የሚያጠናክሩ ሊሆኑ እንደሚገባ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ገለጹ፡፡
በኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት እና በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አዘጋጅነት “መገናኛ ብዙኃን ለአገር ግንባታ” በሚል መሪ ሃሳብ ለፌደራልና ለክልል የመገናኛ ብዙኃን የሥራ ኃላፊዎችና አርታኢያን ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና ተጠናቋል፡፡
መገናኛ ብዙኃን የአገርን ብሔራዊ ጥቅም በማስቀደም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ መሥራት እንዳለባቸው ተመላክቷል፡፡
በማጠቃለያ መርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ፤ መገናኛ ብዙኃን በሕዝቦች መካከል ወንድማማችነት እንዲጸናና አንድነት እንዲጠናከር መሥራት አለባቸው ብለዋል፡፡
መንግሥት የአገርን ብልጽግና ለማረጋገጥ እንደምሰሶ የያዛቸው አቅጣጫዎች ከግብ እንዲደርሱ መገናኛ ብዙኃን የራሳቸውን በጎ አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡
የብዝኃ-ኢኮኖሚው ምሰሶ በሆኑት ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድን እና አይ ሲ ቲ ዘርፎች ላይ ትልልቅ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።
ለአብነትም መንግሥት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ዘመናዊ ግብርናን በማስፋፋት በርካታ ሥራዎች እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
መገናኛ ብዙኃንም ይህ ዕቅድ ከግብ እንዲደርስ ከማገዝ ባሻገር እውነተኛ መረጃዎችን ለሕዝብ ተደራሽ ማድረግ እንዳለባቸውም ገልፀዋል፡፡
በተለይም መንግሥት ሜካናይዜሽንን በመጠቀም በስንዴ ልማት እያከናወነ የሚገኘውን ውጤታማ ሥራዎች ላይ መሥራት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ በሌማት ትሩፋትና አረንጓዴ አሻራ የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት የዘገባዎች ትኩረት ሊሆን ይገባልም ብለዋል፡፡
በሌላ መልኩም በማኑፋክቸሪንግ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም እና የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት እየተሰሩ ባሉ ተግባራት ዙሪያ በስፋት መሥራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡
አካታች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በኢትዮጵያ እንዲረጋገጥ መንግሥት እየሰራ ያለውን በጎ ሥራ ሕዝቡ ተገንዝቦ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ መገናኛ ብዙኃን የሚጠበቅባቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
መገናኛ ብዙኃን ዘላቂና አዎንታዊ ሰላም እንዲረጋገጥ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስቀድሙ ዘገባዎች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
በሕዝብ መገናኛ ብዙኃን የሚሰሩ ዘገባዎች አካታች ሊሆኑ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
መገናኛ ብዙኃን ለምርመራ ጋዜጠኝነት ልዩ ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ለስኬታማነቱ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እድሪስ በበኩላቸው፤ መገናኛ ብዙኃን በዘገባዎቻቸው ለአገር ግንባታ አስተዋጽኦ ለሚያደርጉ ጉዳዮች ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
በዚህም ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችሉ ሚዛናዊ ዘገባዎችን መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ