የማሻ ኤፍ ኤም 103 ነጥብ 8 ራዲዮ ጣቢያ እንዲከፈት መፈቀዱ ለሕብረተሰቡ ወቅታዊ መረጃዎችን ከማዳረስ ባሻገር የልማት ሥራዎችን ለማሳለጥ ፋይዳው የጎላ ነው – የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ

የማሻ ኤፍ ኤም 103 ነጥብ 8 ራዲዮ ጣቢያ እንዲከፈት መፈቀዱ ለሕብረተሰቡ ወቅታዊ መረጃዎችን ከማዳረስ ባሻገር የልማት ሥራዎችን ለማሳለጥ ፋይዳው የጎላ ነው – የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 09/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ሬዲዮና ቴለቭዥን ድርጅት ሸካ ዞን የማሻ ኤፍ ኤም 103 ነጥብ 8 ራዲዮ ጣቢያ እንዲከፈት መፈቀዱ ለሕብረተሰቡ ወቅታዊ መረጃዎችን ከማዳረስ ባሻገር የልማት ሥራዎችን ለማሳለጥ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር ገለጸ።

እስካሁን የነበረውን የተደራሽነት ችግር ለመቅረፍ የሚዲያው ሚና የላቀ መሆኑን የገለጹት የማህበረሰቡ ተወካዮች ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ሚዲያ ለአንድ ማህበረሰብ ንቃተ ህልና መዳበር፣ ባህልና ቋንቋቸው እንዲጎለብት አበርክቶው የጎላ ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ በተለይ የኤፍ ኤም ራዲዮዎቹ በቀላሉ ወደ ማህበረሰቡ የመድረስ አቅማቸው ሰፊ ነው ብለዋል።

ካላቸው የአገልግሎት ስፋት አኳያ መንግስት እነዚህን ራዲዮ ጣቢያዎች በከተማም ሆነ በገጠር ለማዳረስ በትጋት እየሰራ እንደሆነም ተጠቁሟል።

የሸካ ዞን ከዚህ ቀደም ከቦንጋ ኤፍ ኤም 97 ነጥብ 4 ራዲዮ ጣቢያ የሚዲያ ሽፋኑን ሲጠቀም መቆየቱን የገለጹት የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ ከተደራሽነት አኳያ ውስንነት በመኖሩ ጥያቄዎች ሲቀርቡ መቆየታቸውን አስረድተዋል።

ከዚህም የተነሳ በተለያዩ ጊዜያት ሲነሳ የነበረው የሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ በመደረጉ መደሰታቸውን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው ተቋሙ በተሟላ መልኩ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ዞኑ የበኩሉን አስተዋጽዖ ማድረጉን አስረድተዋል።

አገልግሎቱ እየሰፋና እየተጠናከረ እንዲሄድ በቀጣይ የተያዘ እቅድ መኖሩን ገልጸው የዞኑንም ሆነ የክልሉን እምቅ የተፈጥሮ ሐብትና የመልማት አቅም ለማስተዋወቅና ተጠቃሚ ለመሆን ፋይዳው የላቀ መሆኑን አቶ አበበ አመላክተዋል።

በየጊዜው የሚነሳው የሕዝቡ ቅሬታ ተገቢ ምላሽ ማግኘት እንዲችል የዞኑ አስተዳደር 5 ሚሊዮን ብር በጀት በመመደብ ለራዲዮ ጣቢያ የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ ለማሟላት ጥረት ማድረጉን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ዮሐንስ ካሳሁን ናቸው።

ራዲዮ ጣቢያው በሦስቱ የብሄረሰቦች ቋንቋዎች አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን የገለጹት አቶ ዮሐንስ ሕብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት ሚዲያውን በመጠቀም የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን በተሳካ ሁኔታ ማከናወን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ራዲዮ ጣቢያው እንዲከፈት በተደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የድርሻቸውን ለተወጡ አካላት ምስጋና ያቀረቡት አቶ ዮሐንስ ተቋሙ በቀጣይ ከሕብረተሰቡም ሆነ ከመንግስት የሚጠበቅበትን ሃላፊነት እንዲወጣ ድጋፍና ክትትሉ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

ከብሔረሰቡ ተወካዮች መካከል ወልታታ ባህሩ ወልደጊዮርጊስ እንደገለጹት ሚዲያው መፈቀዱ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን፣ ወቅታዊ መረጃዎችንና የሕግ ግንዛቤዎችን ሕዝቡ እንዲያገኝ ያግዛል።

የሕዝቦችን መልካም እሴቶች ከመገንባትና የሌሎችን ልምድና ተሞክሮ ለመካፈል ፋይዳው የላቀ መሆኑን የገለጹት ወልታታ ባህሩ ሚዲያውን በጋራ ማሳደግ ከሁላችንም ይጠበቃል ብለዋል።

ዘጋቢ፡ መለሰ ገብሬ – ከቦንጋ ጣቢያችን