ብዝኃ ህይወትን ቀጣይነት ባለው መንገድ በማልማትና በመንከባከብ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል – አቶ ተፈሪ አባተ

ብዝኃ ህይወትን ቀጣይነት ባለው መንገድ በማልማትና በመንከባከብ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል – አቶ ተፈሪ አባተ

ሀዋሳ፡ መሰከረም 09/2019 ዓ.ም (ደሬቴድ) ብዝኃ ህይወትን ቀጣይነት ባለው መንገድ በማልማትና በመንከባከብ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የሶዶ ክላስተር አስተባባሪና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ አስገነዘቡ።

በጎፋ ዞን በስምንት ሚሊየን ብር የማህበረሰብ ነባር የዕጸዋት ዘር ባንክ ግንባታ ለመጀመር የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የሶዶ ክላስተር አስተባባሪና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ፤ የማህበረሰብ ዘር ባንኩ እየጠፉ ያሉ የእፅዋት፣ የእህልና ሌሎች ነባር ዝርያዎችን በማሰባሰብ፣ በማስጠበቅና በማስተዋወቅ ብዝሃ ሕይወትን ለመጠበቅ ወሳኝ ነው።

ነባር ዘሮችን በማሰባሰብና በተስማሚ ሁኔታ በማከማቸት ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፉ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ብዝኃ ህይወትን ቀጣይነት ባለው መንገድ በማልማት በመንከባከብና ለረዥም ጊዜ በማቆየት ዋናውን ዘር ሳያጠፋ መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል።

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ፤ አካባቢን በቋሚነት ከመንከባከብ ባለፈ እየጠፉ ያሉ ነባር ዘሮችን በመሰብሰብ በተመረጡ አካባቢዎች በማከማቸት ብዝሃ ሕይወትን ለመጠበቅ በርካታ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸዋል።

በሰው ሠራሽና በሌሎች ምክንያቶች የደን ሀብትና የተፈጥሮ ዝርያዎች እየተመናመኑ መሆኑንም አመላክተዋል።

ይህንን ለመከላከልና ነባር ዝርያዎችን ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ የማህበረሰብ ዘር ባንክ ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወትና የአየር ንብረት ለውጥ ፎረም ዋና ዳይሬክተር ግርማ ባልቻ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የተፈጥሮ ሀብትንና ብዝሃ ሕይወትን መጠበቅ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን ገልጸው ማህበረሰቡ በማህበር ተደራጅቶ እየጠፉ ያሉ ነባር ዘሮችን በመሰብሰብና በተመረጡ አካባቢዎች በማስጠበቅ ለብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚችል አስረድተዋል።

ዶ/ር ግርማ አክለውም፤ አገር በቀል ዕፅዋትን መንከባከብ፣ የተፈጥሮ ሀብትን መጠበቅና የነባር ዘሮችን ሀብት ማስቀጠል የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያግዙ ተግባራት መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አየር ንብረት ለውጥና አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቴ ግጄ፣ ነባር ዘሮችን መመዝገብ፣ መጠበቅና መንከባከብ ለቀጣይ ትውልድ የሚተላለፈውን የተፈጥሮ ሀብት ለማስቀጠል ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ግዛቴ፤ ኢትዮጵያ በብዝሃ ሕይወት ሀብቷ የምትታወቅ አገር መሆኗን ጠቁመው በክልሉ በአምስት ዞኖች የነባር ዘር ባንኮች መቋቋማቸውንና በጎፋ ዞንም በተመረጡ ወረዳዎች ነባር ዘሮችን የማስጠበቅ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።

የማህበረሰብ ዘር ባንኩ ነባር የእፅዋትና የእህል ዝርያዎችን ከመጠበቅ ባለፈ፣ ለማህበረሰቡ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ለመፍጠርና የአካባቢውን ተፈጥሯዊ ሀብት ለቀጣይ ትውልድ ለማስቀጠል እንደሚያግዝ ተገልጿል።

አመራሮቹ በገዜ ጎፋ ወረዳ ለፌ የዘር ባንክ የመሰረት ድንጋይ ያሰቀመጡ ሲሆን
የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም አከናውነዋል።

በመድረኩ የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወትና የአየር ንብረት ለውጥ ፎረም፣ የCVM ፕሮግራም፣ የEBI ተወካዮች፣ የክልልና የጎፋ ዞን አመራሮች፣ ባለሙያዎችና የማህበረሰቡ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን