የዘይሴ ብሔር ዘመን መለወጫ “ቡዶ ኬሶ” በዓል በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ኤልጎ ቀበሌ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል

የዘይሴ ብሔር ዘመን መለወጫ “ቡዶ ኬሶ” በዓል በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ኤልጎ ቀበሌ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል

በክብረ በዓሉ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ታደሰ እንዳሉት፤ በጋሞ ዞን ውስጥ ከሚገኙት ሶስቱ ነባር ብሔረሰቦች አንዱ የሆነው ዘይሴ ብሔር አሮጌውን ዓመት ሸኝቶ አዲስ ተስፋ ሰንቆ በአዲስ መንፈስ አዲስ አመት የሚቀበልበት ወቅት ነው።

የዘንድሮውን ቡዶ ኬሶ በዓልን ልዩ የሚያደርገው ባለፉት ጊዜያት በአካባቢው ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር በሠላም ተፈቶ በጥሩ ሁኔታ ላይ በነበረበት ወቅት መሆኑ ነው።

የአካባቢው ወጣቶች ወደ ቀደመ ሠላም እና ልማት ፊታቸውን በመመለስ የመቻቻል ዕሴት ማጎልበት እንዳለባቸው አሳስበዋል አቶ ዳዊት።

የጋሞ ዞን ዋና የመንግሥት ተጠሪ እና የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ገዛኸኝ ጋሞ፤ በጋሞ ዞን የሚገኙ ሶስቱ ነባር ብሔሮች ጋሞ፣ ዘይሴ እና ጊዲቾ በአንድ ዞን ውስጥ ተዋደው እና ተከባብረው የሚኖሩበት ነው።

በሁሉም አካባቢዎች ላይ የሚከበረው የአዲስ ዓመት መለዋጫ የጋራ ዕሴታቸው መሆኑን የተናገሩት አቶ ገዛኸኝ፤ የአብሮነት ዕሴቶችን በማጎልበት የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን በማጠናከር የአካባቢውን ልማትና ሠላም ማጎልበት ይገባናል ብለዋል።

በአባቶች መልካም ምኞት መግለጫ እና ምርቃት የተጀመረው የዘይሴ ብሔር ዘመን መለወጫ ቡዶ ኬሶ በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል።

የአዲስ ዓመት የተስፋ ማብሰሪያ ምልክት የሆነው ደመራ ተለኩሶ በዓሉ ተከብሮ ውሏል።

ዘጋቢ: ወ/ገብርኤል ላቀው – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን