ሆዜ ሞሪንሆ እና ዲዬጎ ሲምዮኔ ከ12 ዓመታት በኋላ በማድሪድ ደርቢ ይፋለማሉ

ሆዜ ሞሪንሆ እና ዲዬጎ ሲምዮኔ ከ12 ዓመታት በኋላ በማድሪድ ደርቢ ይፋለማሉ

የፊታችን እሁድ የእግር ኳስ ተመልካች ዓይኖች ሁሉ ወደ ዋንዳ ሜትሮፖሊታኖ ስቴዲየም ያማትራሉ፡፡ ሁልጊዜም ተናፋቂ የሆነው የማድሪድ ደርቢ በባለሜዳው በአትሌቲኮ ማድሪድ እና በሪያል ማድሪድ መካከል ይካሄዳል፡፡

እንደ ጨዋታው ሁሉ ትኩረት በክረምቱ ወደ በርናባዉ በአሰልጣኝነት ያቀኑት ሆዜ ሞሪንሆ እና በአትሌቲኮው አሰልጣኝ ዲዬጎ ሲምዮኔ ላይ አርፏል፡፡ ሁለቱ አሰልጣኞች ከ12 ዓመታት በፊትም በተመሳሳይ በስፔን ለ3 ዓመታት ተቀናቃኝ ሆነው አሳልፈዋል፡፡

አሁንም ታሪክ ራሱን ደግሟል፡፡ በስፔን ላሊጋ 7ኛ ሳምንት በሳምንቱ መጨረሻ ይፋጠጣሉ፡፡ የስፔኑ ሙንዶ ዲፖርቲቮ ጋዜጣ ስለጨዋታው ባሰፈረው ዘገባ፤ ሁለቱ አሰልጣኞች በተፈቀደላቸው የሜዳው የጎን መስመር ላይ የሚያሳዩት አካላዊ ትዕይንትም እንዲሁ በተመልካቾች በጉጉት እየተጠበቀ ነው፡፡

ሁለቱም አሰልጣኞች ከአውሮፓዊያኑ 2014 በኋላ በጥሩ ብቃት ቡድኖቻቸውን ቢመሩም እርስ በርስ ግን ተገናኝተው አያውቁም፡፡ ሆዜ ሞሪንሆ ከሪያል ማድሪድ በኋላ በነበራቸው የአሰልጣኝነት ቆይታ ማችስተር ዩናይትድ፣ ቶተንሃም፣ ሮማ፣ ፌነርባቼ እና ቤነፊካን አሰልጥነዋል፡፡ ዲዬጎ ሲምዮኔ በበኩላቸው ከአትሌቲኮ ማድሪድ የአሰልጣኝነት መንበር እስካሁን አልለቀቁም፡፡

ሞሪንሆ በማድሪድ ሳሉ ሁለቱ አሰልጣኞች እርስ በርስ ለ6 ጊዜያት ተገናኝተዋል፡፡ ሞሪንሆ በሶስቱ ሲያሸንፉ፤ ሲምዮኔ 2 ጨዋታዎችን ረትተዋል፡፡ በአንዱ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡

ከሁሉም ግን ከተመልካቾች ሕሊና የማይጠፋው በ2013 በኮፓ ዴል ሬይ የፍጻሜ ጨዋታ በሳንቲያጎ በርናባዉ ተገናኝተው በአትሌቲኮ አሸናፊነት የተጠናቀቀው ነው፡፡ ያ የፍጻሜ ጨዋታ ከተካሄደበት 13 ዓመት እና ሞሪንሆ ማድሪድን ከለቀቁበት 12 ዓመታት በኋላ አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ በዋንዳ ሜትሮፖሊታኖ ስቴዲየም ይገናኛሉ፡፡

በዘንድሮ የ2026/27 የውድድር ዘመን በላሊጋው ሆዜ ሞሪንሆ በ6 ጨዋታዎች አምስቱን አሸንፈው በአንዱ በመረታት በደረጃው ሰንጠረዥ 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ዲዬጎ ሲምዮኔ በበኩላቸው በ6 ጨዋታዎች አራቱን አሸንፈው፣ በአንዱ ተረትተው አንዱን አቻ በመውጣት ተከታዩን 3ኛ ደረጃ ይዘዋል፡፡ እሁድ ዕለትም እርስ በርስ በሚፋለሙበት ጨዋታ ምን ሊፈጠር ይችላል የሚለውን የእግር ኳስ ተመልካቹ በጉጉት ይጠብቃል፡፡

ሆዜ ሞሪንሆ አነጋጋሪ በሆነው አስተያየታቸው፣ ዲዬጎ ሲምዮኔ ደግሞ በመጫወቻ ሜዳ ጠርዝ ላይ በሚያደርጉት አስቂኝ አካላዊ እንቅስቃሴ በይበልጥ ይታወቃሉ፡፡


ዘጋቢ፡- ኢያሱ ታዲዎስ