የሀዲያ ብሄር ዘመን መለወጫ “ያሆዴ“ በአልን በዩኒስኮ ለማስመዝገብ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ እንደሆነ ተገለጸ

የሀዲያ ብሄር ዘመን መለወጫ “ያሆዴ“ በአልን በዩኒስኮ ለማስመዝገብ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ እንደሆነ ተገለጸ

ያሆዴ የሀዲያ ብሄር ዘመን መለወጫ በዓል በሀዋሳ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

በበአሉ ላይ የዞኑ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ እቴነሽ ሙሉጌታ፣ የሀዲያ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን ቦጋለ፣ በሀዋሳና አካባቢዋ የሚኖሩ የብሄሩ ተወላጆች ተጋባዥ እንግዶች የተገኙ ሲሆን በአሉ በባህል ሽማግሌዎች ምርቃትና በመልካም ምኞት ተጀምሯል።

በበአሉ ላይ ንግግር ያደረጉት የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሀላፊ አቶ መስፍን ቦጋለ እንዳሉት፤ የሀዲያ የዘመን አቆጣጠር በወቅቶች ላይ መሰረት ያደረገ ሲሆን አዲስ አመት መስከረም ከገባ በሁለተኛው ሳምንት ጀምሮ ይከበራል።

ያሆዴ በዓል ከአሮጌው ወደ አዲስ አመት መሸጋገሪያ ሲሆን የህብረተሰብን አብሮነት፣ ፍቅርና መተሳሰብ የሚጎላበት በዓል ነው ያሉት አቶ መስፍን፤ በዓሉ የወንድማማችነት እና የእህትማማችነት እሴትን በጋራ ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ያሆዴ በዓል ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ የጠቆሙት የመምሪያው ኃላፊ፤ በዓሉን በማይዳሰስ ቅርስ በዮኔስኮ ለማስመዝገብ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የዞኑ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ እቴነሽ ሙሉጌታ በበኩላቸው፤ ያሆዴ በዓል በሀዲያ ብሔር ዘንድ በታላቅ ጉጉት የሚጠበቅ እና አሮጌውን ዘመን ወደ አዲሱ ዘመን በይቅርታና በእርቅ መሸጋገሪያ ድልድይ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በሁሉም ዕድሜ ክልል የሚገኙ የሀዲያ ተወላጆች ያሆዴ በዓልን በተለያዩ ዝግጅቶች የሚያከብሩት በዓል ነው ያሉት አፈ ጉበኤዋ፤ በዓሉ የማህበረሰብን የእርስ በርስ መስተጋብር የሚያጠናክር በመሆኑ መተባበር፣ መከባበር፣ ፍቅር፣ ሰላም፣ በአብሮነት መኖር በያሆዴ የሚንፀባረቁ ትሩፋቶች ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።

የሀዲያ ዞን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ እቴነሽ ሙሉጌታ የኦሮሚያ ብሔር አባገዳዎችና ሀደ ስንቄዎች፣ የሲዳማ የባህል ሽማግሌዎች፣ ከሻሸመኔ፣ ከወንዶገነት፣ ከኩየራ እና ከአርሲ ነገሌ የመጡ የሀዲያ፣ የሲዳማና የኦሮሚያ ባህል ሽማግሌዎች፣ ተወላጆችና ልዩ ልዩ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በበዓሉ ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ መለሰች ዘለቀ