ከ 2 ሺህ በላይ ወጣቶች የተሳተፉበት የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በስኬት ተጠናቋል – የበና ጸማይ ወረዳ አስተዳደር

ከ 2 ሺህ በላይ ወጣቶች የተሳተፉበት የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በስኬት ተጠናቋል – የበና ጸማይ ወረዳ አስተዳደር

ሀዋሳ፡ መስከረም 07/2019 ዓ.ም (ደሬቴድ) በተመረጡ 20 የትኩረት መስኮች ከ 2 ሺህ 150 በላይ ወጣቶችን አሳትፎ ሲከናወን የቆየው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በስኬት መጠናቀቁን በደቡብ ኦሞ ዞን የበና ጸማይ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ።

በ34 ቀበሌያት በተከናወነው አገልግሎትም ከ 27 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ገንዘብ ማዳን መቻሉም ተመላክቷል።

በወረዳው የ2018 የወጣቶች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አፈጻጸም የተገመገመበት የማጠቃለያ መርሃ ግብር በቀያፈር ከተማ ተካሂዷል።

በአርብቶ አደሩ አካባቢ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ባህሉን ለማዳበር ሰፊ ስራዎች ሲከናወኑ የቆዩ ሲሆን በበና ጸማይ ወረዳም ስራው በትኩረት ሲከናወን ቆይቷል።

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዮሐንስ ገርሾ በ2018 ዓ.ም የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተመረጡ 20 የትኩረት መስኮች ሲከናወን መቆየቱን ጠቅሰው፤ በዚህም ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ለአብነትም አቅመ ደካሞችን ከመደገፍ ረገድ 63 ቤቶች መገንባት እና 33 ቤቶች ማደስ መቻሉን ጠቅሰው፤ በማዘጋጃ ቤት ደረጃም 6 የብሎኬት ቤቶች ተገንብተው ለነዋሪዎች መተላለፋቸውን አብራርተዋል።

አያይዘውም በበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ 33 የገጠር ቤቶችን በማደስና ቁሳቁስ የማሟላት ስራዎች ትኩረት የተቸራቸው እንደሆኑም አንስተዋል።

ከዚህም ባሻገር በትምህርት፣ ጤናና ግብርና መስኮች የተለያዩ ስራዎች የተከናወኑ ሲሆን በደም ልገሳ መርሃ ግብርም ከ43 ዩኒት በላይ ደም ማሰባሰብ ተችሏል ብለዋል።

በአጠቃላይ ተግባሩ በገንዘብ ሲተመን ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ የሚደርስ መሆኑንም ጠቁመዋል።

አገልግሎቱ በአካባቢው ባህል እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ በርካቶች ተሳትፈውበታል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ ተግባሩ በበጋውም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ አሳስበዋል።

የወረዳው የወጣቶች ጉዳይና የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጎላ ጨዌ በበኩላቸው፤ በወረዳው በአገልግሎቱ 24 ሺህ ወጣቶችን በማሳተፍ 60 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ገልፀዋል፡፡

የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በተከናወነባቸው 34 ቀበሌያት የአፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት የተካሄደ ሲሆን ተሳታፊዎችም የተገኘውን ስኬት በበጋ ወቅትም ማስቀጠል ይገባዋል ብለዋል።

በተግባሩ የተሻለ አፈጻጸም ያሳዩ ቀበሌያት፣ ተቋማትና ግለሰቦችም የእውቅና ሰርተፊኬትና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ዘጋቢ፡ ወንድሜነህ አድማሱ – ከጂንካ ጣቢያችን