በካርበን ግብይት እና ሥነ-ምህዳር አገልግሎት ክፍያ ላይ ትኩረት ያደረገ ሥልጠና ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባለድርሻ አካላት ተሰጠ

በካርበን ግብይት እና ሥነ-ምህዳር አገልግሎት ክፍያ ላይ ትኩረት ያደረገ ሥልጠና ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባለድርሻ አካላት ተሰጠ
‎
‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ከኢፌዲሪ ፕላንና ልማት ሚኒስቴርና ከኢፌዲሪ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመተባበር በካርበን ገበያ እና በሥነ ምህዳር አገልግሎት ክፍያ ላይ ትኩረት ያደረገ ሥልጠና ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባለድርሻ አካላት ሰጥቷል።
‎
‎ሥልጠው በቀጣይ በካርበን ገበያ እና በሥነ ምህዳር አገልግሎት ክፍያ ላይ በሚሠሩ ሥራዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ቴክኒካል ስልጠና መሆኑ ተመላክቷል።
‎
‎የክልላችን ህዝብ ኢኮ ሲስተሙን ሲጠብቅ የቆየ ቢሆንም ከዘርፉ ተጠቃሚነት አንጻር ብዙ ጥያቄ ሲነሳበት የነበረ መሆኑን እና ስልጠናው ይህንን ጥያቄ የሚመልስ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአካባቢ ጥበቃ እና የአየር ንብረት ለውጥ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቴ ግጄ ተናግረዋል።
‎
‎ችግሩን ለመቅረፍ የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ አውጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸው በተዘረጋው አሠራር መሠረት የሚሠራ ሥራ መሆኑን አመላክቷል።
‎
‎እንደ ክልል አሠራሩን ወደ ታች ለማውረድ የተዘጋጀ የአሰልጣኞች ስልጠና መሆኑንም አስረድተዋል።
‎
‎በተለይ የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎች ጤናማ እና ንጹህ የሆነ አካባቢ እንዲኖራቸው ለማድረግ በአረንጓዴ አሻራ፣ በወንዝ ዳር ልማት፣ ጽዱ ኢትዮጵያን እንገንባ በሚል እና በኮሪደር ልማት የተለያዩ ኢኒሼቲቮችን በመቅረጽ ሲሠራ መቆየቱን አንስተዋል።
‎
‎ሥነ ምህዳራችንን የምንጠብቀው ለአካባቢ ጥበቃ ሥራ ብቻ ሳይሆን በቀጣይ ጥቅም ላይ ሊውል በሚችል አግባብ ላይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ የተዘጋጀ ሥልጠና መሆኑን አስረድተዋል።
‎
‎የሥልጠናው ተሳታፊዎች በክልላችን በሁሉም ዞኖች ያሉ ደኖች እና ሥነ ምህዳር ወደ ክፍያ እንዲገባ የተደራጀ መረጃ በአግባቡ በመያዝ እና በማደራጀት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።
‎
‎በፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የአካባቢ ህግ እና ደረጃዎች ዴስክ ኃላፊ አቶ ወንደሰን ታደሰ÷ በታህሳስ ወር 2018 ዓ.ም በኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ በሥራ ላይ በዋለ በሥርዓተ ምህዳር አገልግሎት ክፍያ አዋጅ መነሻ አዋጁ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
‎
‎አክለውም ስልጠናው ለአሰልጣኞች የተዘጋጀ እንደመሆኑ የአዋጁን አፈጻጸም የተሻለ ለማድረግ አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

‎
‎ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የወላይታ እና የጌዴኦ ዞን አካባቢ ጥበቃ እና የአየር ንብረት ቁጥጥር ጽ/ቤት ኃላፊዎች አቶ መርክነህ ማለዳ እና አቶ ስጦታ ገመደ በሰጡት አስተያየት÷ ስልጠናው ከዚህ ቀደም በዘርፉ ሲያከናወኑ የነበሩ ተግባራት በወጣው አዋጅ አስደግፈው እንዲሄዱ እና ክፍተቶችን እንዲያርሙ አቅም የሚፈጥር እንደሆነ አመላክተዋል።
‎
‎በስልጠናው የዞን፣ የሪጂኦ ፖሊሲ ከተሞች አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ጽ/ቤት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
‎
‎ዘጋቢ: እንግዳየሁ ቆሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን