የተሳፋሪዎችን ደህንነትና ምቾት ለማስጠበቅ የትራንስፖርትና የትራፊክ ፖሊስ አካላት ቁጥጥራቸውን አጠናክረው መቀጠላቸው ተገለጸ
የአዲስ ዓመት በዓልን ተከትሎ የሚኖረውን የተሳፋሪ ፍሰት በሰላምና በተመቻቸ ሁኔታ ለማስተናገድ የትራንስፖርትና የትራፊክ ፖሊስ አካለት የቁጥጥር ሥራ አጠናክረው መቀጠላቸውን የከምባታ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ አስታወቀ።
የተሳፋሪ መብት ጥበቃ፣ የትርፍና ታሪፍ ቁጥጥር፣ የተሽከርካሪ ምርመራና ቁጥጥር እንዲሁም የትራፊክ አደጋ መከላከል ትኩረት ከተሰጣቸው ሥራዎች መካከል መሆናቸውም ተመላክቷል።
የከምባታ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ምክትል ሀላፊና የትራንስፖርት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ታደሰ አቦዬ እንደገለጹት፣ የአዲስ ዓመት በዓልን ተከትሎ የሚኖረውን የተሳፋሪ ፍሰት በተገቢው ሁኔታ ለማስተናገድ የተለያዩ ዝግጅቶች ተደርገዋል።
በዚህም ከ800 በላይ ተሽከርካሪዎች በበዓሉ ወቅት የሚኖረውን የተሳፋሪ ፍሰት ለማስተናገድ ዝግጁ መደረጋቸውን አቶ ታደሰ ተናግረዋል።
ከተሽከርካሪ ዝግጅት በተጨማሪ የትራንስፖርት አገልግሎቱ በሥርዓት እንዲከናወን፣ ተሳፋሪዎች መብታቸው እንዲከበር እና ከተገቢው ታሪፍ ውጭ ክፍያ እንዳይጠየቅ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ከትርፍና ታሪፍ ጋር ተያይዞ ሕግና መመሪያን በሚጥሱ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ ሲወሰድ መቆየቱን የጠቆሙት ሀላፊው፣ በ2018 ዓ.ም. ከትርፍና ታሪፍ ጋር በተያያዘ በ116 ሺህ 872 ተሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱንና 14 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ለዞኑ ፋይናንስ ገቢ መደረጉን ገልጸዋል።
ተሳፋሪዎች ከትራንስፖርት አገልግሎት፣ ከታሪፍ ብሎም ከሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ ችግር ካጋጠማቸው ጉዳዩን ለሚመለከታቸው አካላት በማሳወቅ መብታቸውን እንዲያስከብሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የከምባታ ዞን ትራፊክ ዲቪዥን ሀላፊ ኮማንደር ገበየው ካሳ በበኩላቸው፣ የአዲስ ዓመት በዓል መቃረቡን ተከትሎ ወደ አካባቢው የሚገቡና ከአካባቢው የሚወጡ ሰዎች ቁጥር እንደሚጨምር ገልፀው ይህንን የተሳፋሪና የተሽከርካሪ ፍሰት ተከትሎ ሊከሰቱ የሚችሉ የትራፊክ አደጋዎችን ለመከላከል በግብረ ኃይል የተደራጀ ሥራ መጀመሩን አስረድተዋል።
በእያንዳንዱ መናኸሪያም ለተሳፋሪዎችና ለአሽከርካሪዎች ግንዛቤ እየተሰጠ ሲሆን፣ የትራፊክ ሕጎችን በማስከበር አደጋን መከላከል ላይም ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል።
በበዓላት ወቅት የሰዎች እንቅስቃሴ ስለሚጨምር የትራፊክ አደጋ ቁጥሩ ሊያሻቅብ እንደሚችል ያነሱት ሀላፊው አሽከርካሪዎች የፍጥነት ገደብን በማክበር፣ ተሳፋሪዎችም የትራፊክ ሕጎችን በመከተል ለአደጋ መከላከል የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ተሳፋሪዎች መብታቸውን የመጠየቅና ጥሰት ሲያጋጥማቸው የማሳወቅ ባህል አነስተኛ መሆኑን ያነሱት ኮማንደር ገበየው፣ ተሳፋሪዎች ችግር ሲያጋጥማቸው ዝም ከማለት ይልቅ መብታቸውን ለማስከበር ጥሰቶችን ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የተሳፋሪዎችን መብት ማስከበር፣ የተሽከርካሪዎችን ሕጋዊነት መቆጣጠርና የትራፊክ አደጋን መከላከል የአንድ አካል ሥራ ብቻ ሳይሆን የሁሉም የጋራ ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑንም ገልጸዋል።
በበዓሉ ወቅት የሚኖረውን የተሳፋሪ ፍሰት በአግባቡ ለማስተናገድ አሽከርካሪዎችም በቅንነትና በኃላፊነት ሕዝቡን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ሌሎች አሽከርካሪዎችም የትራፊክ ሕጎችን በማክበር፣ የተሳፋሪዎችን መብት በመጠበቅና ከተገቢው ታሪፍ ውጭ ክፍያ ከመጠየቅ በመቆጠብ ሕዝቡን በአግባቡ ሊያገለግሉ እንደሚገባ መልክታቸውን አስተላልፈዋል።
በዱራሜ መናኸሪያ ወደ ሺንሺቾ እና ሆሳዕና ከተሞች ሲጓዙ ያገኘናቸው ተሳፋሪዎች፣ እስካሁን ባደረጉት ጉዞ በታሪፍም ሆነ በተሽከርካሪ አቅርቦት ችግር እንዳልገጠማቸው ገልጸዋል።
በቀጣይ ባሉ ጊዜያትም ችግሮች እንዳያጋጥሙ የክትትልና ቁጥጥር ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸውም ብለዋል።
ዘጋቢ: ረዚቃ ተመስገን – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
ጳጕሜን 5 “የነገው ቀን” በኮሬ ዞን በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው
በክልሉ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ፋና ወጊ ለውጥ ለማስመዝገብ በመሰራቱ አበረታች ለውጦች ተመዝግበዋል – አቶ ጥላሁን ከበደ
በካርበን ግብይት እና ሥነ-ምህዳር አገልግሎት ክፍያ ላይ ትኩረት ያደረገ ሥልጠና ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባለድርሻ አካላት ተሰጠ