የአንድ ማህበረሰብ ቋንቋ ለትውልድ እንዲተላለፍ እና በጽሑፍ እንዲበለጽግ የቋንቋ ሰዋሰው ጥናት ወሳኝ ሚና አለው – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ባህልና ስፖርት ቢሮ

የአንድ ማህበረሰብ ቋንቋ ለትውልድ እንዲተላለፍ እና በጽሑፍ እንዲበለጽግ የቋንቋ ሰዋሰው ጥናት ወሳኝ ሚና አለው – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ባህልና ስፖርት ቢሮ

የአንድ ማህበረሰብ ቋንቋ ሥርዓት ኖሮት ለትውልድ እንዲተላለፍ እና በጽሑፍ እንዲበለጽግ ለማድረግ የብሔረሰብ ቋንቋ ሰዋሰው ወሳኝ ሚና እንዳለው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ባህልና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

‎

‎ቢሮው በደቡብ ኦሞ ዞን የባኔና የቦዲ ብሄረሰቦች ቋንቋ ሰዋሰው ጥናት የማህበረሰብ ትችት መድረክ  በዲመካ ከተማ አካሂዷል።

‎

‎የቢሮው ምክትል እና የባህል ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታሪኩ ኦይቻ፤  የብሔረሰብ ቋንቋ ሰዋሰው ለአንድ ማህበረሰብ ማንነት፣ ባህል እና ግንኙነት ወሳኝ መሠረት በመሆኑ  ቋንቋው ሥርዓት ኖሮት ለትውልድ እንዲተላለፍ እና በጽሑፍ እንዲበለጽግ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።

‎

‎ከዚህ ቀደም በክልሉ ያሉ የአንዳንድ ብሄረሰብ ቋንቋዎች በተለያዩ የዩኒቨርስቲ ምሁራንና ተመራማሪዎች ጥናት ተደርጎባች ለትምህርት አገልግሎት መዋላቸውን ጠቅሰው፤ በደቡብ ኦሞ ዞን ካሉ 15 የብሄረሰብ ቋንቋዎች የባኔና የቦዲ ብሄረሰብ ቋንቋ ለትምህርት አገልግሎት እንዲውል የተከናወነው የሰዋስው ጥናት በማህበረሰቡ በማስተቸትና በማረም ታትሞ አገልግሎት ላይ እንዲውል እየተሰራ ነው ሲሉ ገልፀዋል።

‎

‎የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳደር ልዩ አማካሪ አቶ ዮናታን ሰይድ በበኩላቸው፤ በዞኑ በርካታ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያላቸው የቱሪስትን ቀልብ የሚስቡ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ፀጋዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በጥናት ባለመደገፋቸው ለዞኑም ሆነ ለሀገር ያላቸው  ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ዝቅተኛ ሆኖ መቆየቱን አንስተዋል።

‎

‎በባኔና በቦዲ ማህበረሰብ ዙሪያ የተካሄደው የቋንቋ ስዋሰው ጥናት የብሄረሰቡ ተወላጆች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ ከማድረጉ ባሻገር በአከባቢው ያሉ ቋንቋዎች  ውስጥ  ያሉ የቃላት መወራረስን የሚያስቀርና ቋንቋዎች እንዳይጠፉ የሚታደግ በመሆኑ የተጀመሩ ጥናቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የዞኑ መንግስት የበኩሉን አስተዋፅኦ ያበረክተል ብለዋል።

‎

‎የደቡብ ኦሞ ዞን ባህልና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሉቱርሲ ካሬ የክልሉ ባህልና ስፖርት ቢሮ ከሀዋሳ ዩኒቨርስቲ መምህራንና ተመራማሪዎች ጋር በመተባበር ላደረጉት የባኔና የቦዲ ቋንቋ ሰዋሰው ጥናት አመስግነው፤ በቀጣይ በዞኑ ውስጥ ያልተጠኑና በመጥፋት ላይ ያሉ  ቋንቋዎች ላይ ጥናቶች እንዲካሄዱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመስራት ማህበረሰቡ በራሱ ቋንቋ እንዲማር ለማድረግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

‎

‎የጥናት ፅሁፉን ካቀረቡ መካከል በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የስነ ልሳንና ስነ ተግባቦት መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ፈቀደ ሚኖታ እንዳሉት፤ የቋንቋ ሰዋሰው የአንድን ቋንቋ ስልታዊ ህጎች፣ መዋቅሮች እና ስነ-ስርዓቶች የሚያጠና መሆኑን ጠቁመው፤ የቋንቋን ህልውና በመጠበቅ በሂደት እንዳይቀላቀል እና እንዳይጠፋ እንደሚረዳ አስረድተዋል፡፡

የባኔና የቦዲ ብሄረሰብ ቋንቋ ሰዋሰው ጥናት አልቆ መተቸቱን እና የተነሱ ሃሳብና አስተያየቶች ታርመው አገልግሎት ላይ እንዲውሉ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ ተናግረዋል።

‎‎የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት እንደነዚህ አይነት ጥናቶች ባለመካሄዳቸው የአከባቢው ማህበረሰብ በራሱ ቋንቋ ሳይማር መቆየቱን አንስተው፤ አሁን የእድሉ ተጠቃሚ በመሆናቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል።

‎‎‎አዘጋጅ :-በናወርቅ መንግስቱ

‎