የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ብዝሃነትን በማስተናገድ ሀገራዊ አንድነትን ከማረጋገጥ ረገድ ትልቅ አበርክቶ እንዳለው ተገለፀ

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ብዝሃነትን በማስተናገድ ሀገራዊ አንድነትን ከማረጋገጥ ረገድ ትልቅ አበርክቶ እንዳለው ተገለፀ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት የብሄረሰቦች ምክር ቤት 21ኛው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓልን አስመልክቶ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ በወልቂጤ ከተማ ተካሄዷል።

የክልሉ ብሄረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ እያሱ ተረፈ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም የኢፌድሪ ሕገ መንግስት የፀደቀበት እና በሀገሪቱ ታሪክ ብዝሃነትን በማስተናገድ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና የተረጋገጠበት በመሆኑ በየዓመቱ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ገልፀዋል፡፡

21ኛው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል “በብዝሃነት የደመቀች በምክክር የፀናች ስልጡን ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል የፊታችን ህዳር 29/2019 ዓ.ም በጅማ ከተማ እንደሚከበር አስታውቀዋል።

ህዳር 29 ቀን ብዝሃነትን በማስተናገድም ሆነ ዴሞክራሲያዊ አገራዊ አንድነትን ከማረጋገጥ አንፃር የበዓሉ መከበር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው አብራርተዋል።

20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በክልሉ አስተናጋጅነት በደማቅ ሁኔታ መከበሩን አፈ ጉባኤው አስታውስተው፤ በክልሉ መከበሩ በሁሉም ከተሞች ከፍተኛ የመሰረተ ልማት መነቃቃትን መፍጠር እንዳስቻለም አቶ እያሱ አንስተዋል፡፡

በዚህ ዓመትም 21ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል “በብዝኃነት የደመቀች በምክክር የፀናች ስልጡን ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚከበር ዋና አፈ ጉባኤው ገልጸዋል።

በክልሉ በሁሉም መዋቅሮች እና በሰባቱም የክልል ክላስተር ማዕከላት በተለያዩ ሁነቶች ከህዳር 1/2019 ጀምሮ በደማቅ ሁኔታ ይከበራል ሲሉ ተናግረዋል።

በዓሉን አስመልክቶ በየደረጃው የሚከናወኑ ዝግጅቶች አካታች፣ ሕዝባዊ፣ የተቀናጁና የበዓሉን መልዕክት የሚያስተላልፉ እንዲሆኑ ሁሉም አካላት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አቶ እያሱ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ነኢማ ሙኒር በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ህብረ ብሔራዊነትን በማጠናከር ጠንካራ ሀገር በመገንባት ረገድ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ዓላማውም መሪ ቃሉም የመደመር መንግስት እሳቤን መነሻ ያደረገ እንደሆነ አንስተው፤ የመደመር እሳቤ ያለንን ጸጋ መለየትን እንደሚያስቀድም እና የለየነውን ጸጋ መጠቀም ወቅቱ የሚፈልገው ዋነኛ ጉዳይ ሲሉ ገልፀዋል።

ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን እና የወንድማማችነት እሴቶቻችን በጠንካራ መሰረት ላይ መገንባት የሚያስችል በዓል መሆኑንም አስረድተዋል።

ያሉንን ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ ማህበረሰባዊ እሴቶች በማስተዋወቅ ረገድ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር ጠቅሰው፤ በዓሉ ሀገራዊ መግባባት፣ የህዝብ ለህዝብ ትስስር በማጠናከር ረገድ ዓይነተኛ ሚና ይጫወታልም ነው ያሉት።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፤ የብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል በየዓመቱ መከበሩ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አንስተው፤ በተለይ ባለፈው ዓመት ለ20ኛ ጊዜ የተከበረው በዓል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ ከማጠናከር በተጓዳኝ የክልሉን ልማት በማነቃቃት ረገድ ዓይነተኛ ሚና መጫወቱን አውስተዋል።

የመድረኩ መዘጋጀት ከዚህ ቀደም የነበሩ በጎ ተሞክሮዎችን በማስፋት በዓሉን በተሻለ መልኩ ለማክበር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።

ዘጋቢ፡ መሀመድ ሽሁር – ከወልቂጤ ጣቢያችን