ከፋፋይ ከሆኑ አጀንዳዎች በመራቅ ህብረታችንን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ

ከፋፋይ ከሆኑ አጀንዳዎች በመራቅ ህብረታችንን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ጳጉሜ 04/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከፋፋይ ከሆኑ አጀንዳዎች በመራቅ ህብረታችንን ማጠናከር አለብን ሲሉ የካፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ደመላሽ ንጉሴ ገለጹ።

ጳጉሜን 4 የህብር ቀን “የኢትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል መሪ ቃል በቦንጋ ከተማ ተከብሯል።

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የካፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ደመላሽ ንጉሴ በኢትዮጵያ ያሉ የሃይማኖት፣ የቋንቋና የብሄር ብዝሃነት ውበታችን በመሆናቸው ልንጠብቃቸውና ልንጌጥባቸው ይገባል ብለዋል።

እነኚህን እሴቶች የውበታችን መገለጫ በመሆናቸው ሊከፋፍሉን ከሚችሉ አጀንዳዎች በመራቅ ህብረታችንን ማጠናከር አለብን ያሉት ኃላፊው፥ ኢትዮጵያዊያን ከውስጥና ከውጭ የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመሻገር ህብረታቸው ትልቁን ሚና ተጫውቷል ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያን ህብረ ብሔራዊነት የሚያረጋግጡ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል ያሉት አቶ ደመላሽ ሀገራዊ ምክክር እና የህዳሴ ግድብን ለአብነት አንስተዋል።

ህብረታችንን በማጉላት ለሀገራችን አንድነት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

የካፋ ዞን ባህል፤ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ሀላፊ ወይዘሮ ታርኳ ታከለ የሚዲያ አጠቃቀማችን አንድነትንና ህብረትን በሚፈጥር መልኩ መሆን እንዳለበት አስገንዝበው፥ ሕብረት ለሰላምና ለልማት መሠረት በመሆኑ የሕዝቦችን አብሮነት፣ መተሳሰብና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር ሊውል እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዕለቱን አስመልክቶ ሰነድ ያቀረቡት የካፋ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዳሙ እሸቱ የኢትዮጵያን ህብረ-ብሔራዊ አንድነት እና አብሮነት ለማጠናከር የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተቋማት ድርሻ ትልቅ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአብሮነት እሴቶችን የሚያጎሉ፣ እውነተኛና ወቅታዊ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ ከተሳተፉት መካከል አቶ ወንድሙ ማሞ እና ወይዘሮ መዓዛ ሀይለማሪያም በሰጡት አስተያዬት አባቶቻችን በህብረት ቆመው በጠላት ያልተደፈረች ሀገር አስረክበውናል ብለዋል።

የአሁኑ ትውልድም ይህንን ህብረት ከማስቀጠል ባሻገር የመደጋገፍና የመረዳዳት ባህላችንን በማጠናከር ለተቸገሩ ወገኖች መድረስ ይጠበቅብናል ሲሉ ገልጸዋል።

በፕሮግራሙ የቦንጋ ትምህርት ኮሌጅ የኢኮኖሚ አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች የሚሆን የትምህርት ቁሳቁስ ስጦታ አበርክቷል።

ዘጋቢ፡ ግርማ ቆጭቶ – ከቦንጋ ጣቢያችን