ማንቼስተር ዩናይትድ የመጀመሪያ ድሉን ፍለጋ ከኢፕስዊች ጋር ይፋጠጣል
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 2ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ በጉጉት በሚጠበቁ አራት ጨዋታዎች ይቀጥላል።
ትኩረትን በይበልጥ በሳበው ምሽት 12፡30 ጨዋታ ማንቼስተር ዩናይትድ በታሪካዊው ኦልድትራፎርድ ስታዲየም ኢፕስዊች ታውንን ያስተናግዳል።
በመጀመሪያው ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ከ9 ዓመታት በኋላ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በተመለሰው ሃል ሲቲ ያልተጠበቀ ሽንፈት የገጠመው ማንቼስተር ዩናይትድ፣ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል ለማስመዝገብና በከፍተኛ ዝግጅት ወደ ሜዳ ይገባል።
በአሰልጣኝ ማይክል ካሪክ የሚመሩት «ቀያይ ሰይጣኖቹ» በ2025/26 የውድድር ዘመን ያሳዩትን መሻሻል ዘንድሮም አጠናክረው ይቀጥላሉ ተብሎ ቢጠበቅም፣ በሃል ሲቲ የደረሰባቸው ሽንፈት በቡድኑ ብቃት ላይ በርካታ ጥያቄዎችን አስነስቷል።
በክረምቱ የዝውውር መስኮት አንድሬይ ሳንቶስ፣ ካርሎስ ባሌባ እና ዮሪ ቴሊማንስን በማስፈረም የመሃል ክፍሉን ያጠናከረው ዩናይትድ፣ አዲሶቹን ተጫዋቾች ከነባሮቹ ጋር በማዋሃድ ጠንካራ የጨዋታ መንገድ ይዞ እንደሚቀርብ ይገመታል።
ሆኖም ለዛሬው ጨዋታ አማድ ዲያሎ እና አዲሱ ፈራሚ ካርሎስ ባሌባ በጉዳት ምክንያት የማይሰለፉ መሆናቸው ለካሪክ ተጨማሪ ፈተና ሆኗል።
በሌላ በኩል በመጀመሪያ ሳምንት ሰንደርላንድን ማሸነፍ የቻለው ኢፕስዊች ታውን፣ ተከታታይ ሁለተኛ ድሉን ለማስመዝገብ በራስ መተማመን ወደ ኦልድትራፎርድ ያመራል።
የዕለቱ ሌሎች ተጠባቂ ጨዋታዎች ስንመለከት በአሰልጣኝ ዣቢ አሎንሶ የሚመራው ቼልሲ በስታምፎርድ ብሪጅ ብራይተንን ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ያስተናግዳል።
ሁለቱም ክለቦች በመጀመሪያው ሳምንት ድል ያስመዘገቡ በመሆናቸው ተከታታይ ድላቸውን ለማስቀጠል የሚያደርጉት ፍልሚያ በከፍተኛ ጉጉት ይጠበቃል።
ዘንድሮ ከአውሮፓ መድረክ ውጭ የሆነው የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ፣ ሙሉ ትኩረቱን በፕሪሚየር ሊጉ ላይ በማድረግ ጠንካራ ፉክክር ያደርጋል ተብሏል።
ሊድስ ዩናይትድ ከ ብሬንትፎርድ እንዲሁም ሰንደርላንድ ከ ፉልሃም በተመሳሳይ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።
የሳምንቱ መርሃ ግብር ነገ ሲጠናቀቅ ምሽት 4፡00 ላይ አስቶንቪላ በቪላ ፓርክ አርሰናልን የሚያስተናግድበት ጨዋታ የሳምንቱ ታላቅ ፍልሚያ እንደሆነ ይታመናል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
ቼልሲ ኤሚሊያኖ ማርቲኔዝን አስፈረመ
ሚካኤል አርቴታ ለአርሰናል 250ኛ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታቸውን ሊመሩ ነው
የሊቨርፑል እና ኖቲንግሃም ፎረስት ጨዋታ 2 አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቀቀ