‎ጷጉሜ 4 የህብር ቀንን በማስመልከት ለአቅመ ደካሞች የበዓል ድጋፍ ተደረገ

‎ጷጉሜ 4 የህብር ቀንን በማስመልከት ለአቅመ ደካሞች የበዓል ድጋፍ ተደረገ

‎ጷጉሜ 4 የህብር ቀንን በማስመልከት የይርጋጨፌ ወረዳ አስተዳደር ከወረዳው የተለያዩ ቀበሌያት ለተውጣጡ አቅመ ደካሞች የበዓል ድጋፍ አደረገ።

‎ድጋፉን ያደረገው የይርጋጨፌ ወረዳ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት፥ በዓሉን በማሰብ በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን ለመርዳት ድጋፍ መደረጉ ተገልጿል።

‎የይርጋጨፌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ቡኔ፥ ጷጉሜ 4 የህብር ቀንን ስናከብር ካለን ላይ ብቻ ሳይሆን ከሌለንም ቢሆን በመካፈልና እርስ በርስ በመደጋገፍ በዓሉን ማክበር እንደሚገባ ገልጸዋል።

‎በዓሉ ያለው ለሌለው በመስጠት፣ ችግረኛ ወገኖችን በማሰብና በመደጋገፍ እንዲከበር ጥሪ ያቀረቡት አስተዳዳሪው፥ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ለሚከሰቱ ችግሮችም ፈጣሪ ዝናብ በምህረቱ እንዲያወርድ ሁሉም ዜጋ በጸሎትና በምልጃ እንዲሳተፍ ጠይቀዋል።

‎የይርጋጨፌ ወረዳ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ትዕግስት ያያ በበኩላቸው፣ ከወረዳው የተለያዩ ቀበሌያት ለተወጣጡ አቅመ ደካሞች የበዓል ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

‎የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብና ከሚኖረን ላይ በመካፈል በዓሉን በህብረት ማክበር እንደሚገባም ለህብረተሰቡ ጥሪ አቅርበዋል።

‎የበዓሉ ድጋፍ የተደረገላቸው የማህበረሰብ ክፍሎችም ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው፣ ሌሎችም በየአካባቢያቸው ተመሳሳይ የመደጋገፍ ተግባር እንዲያከናውኑ ጠይቀዋል።

‎ዘጋቢ: ውብሸት ካሳሁን – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን