በሀድያ ዞን ጎምቦራ ወረዳ ሀብቾ ከተማ ነዋሪ ለሆኑ አንዲት አቅመ ደካማ እናት የመኖሪያ ቤት ርክክብ ተደረገ
ሀዋሳ፡ ጳጉሜ 04/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ማዕድንና ኢነርጂ ኤጄንሲና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በሀድያ ዞን ጎምቦራ ወረዳ ሀብቾ ከተማ ነዋሪ ለሆኑ አንዲት አቅመ ደካማ እናት የመኖሪያ ቤት ገንብቶ አስረከበ።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ማዕድንና ኢነርጂ ኤጄንሲና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አመራሮችና ሠራተኞች በሀድያ ዞን ጎምቦራ ወረዳ ወረዳ ነዋሪ ለሆኑት ወይዘሮ አደነች ሀፌቦ የመኖሪያ ቤት ግንባታ አጠናቀው በዛሬ እለት የቁልፍ ርክክብ አድርገዋል።
በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ኤጄንሲና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አመራሮች እና ሰራተኞች የተገኙ ሲሆን፥ የቤት ውስጥ ቁሳቁስ ለአልጋ፣ ለፍራሽ፣ ለሶፋ ወንበር እንዲሁም ለምግብ ማብሰያ የጤፍ እህልና ዘመናዊ የንብ ቀፎ ድጋፍ መደረጉም ተጠቁሟል።
በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ማዕድንና ኢነርጂ ኤጄንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መኮንን መኔዶ፤ በጎነት ለታይታ የሚደረግ ሳይሆን ቃል በተግባር የሚገለጽበት እና ለአቅመ ደካሞች የሚደረግ መልካም ስራ በሰማይም ዋጋ ያለው በመሆኑ ነው ብለዋል።
ይህ በጎ ተግባር እንዲስፋፋና በተቀናጀ መንገድ እንዲመራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ያስጀመሩት ኢንሼቲቭ መሆኑን አስታውሰው፤ ተግባሩ ብልጽግና ፓርቲ ሰው ተኮር መሆኑንና በርካቶች አንገታቸውን ቀና እንዲያደርጉ በግልፅ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በጎ ተግባር የወደቁ ሰዎች እንዲነሱ፣ የሚለብሱትና መጠለያ አጥተው እንዳይቸገሩ፣ ያለው ለሌለው እንዲያካፍል የሚያደርግ መልካም ተግባር ስለመሆኑም አቶ መኮንን ጠቅሰው ፤ ይህን በጎ ተግባር በሁሉም አካባቢ አጠናክሮ ማስቀጠልን ባህል ማድረግ ይገባል ሲሉም አመልክተዋል።
ግንባታውን በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ እንዲቻል አመራሩና ሠራተኞች በቅንጅት መስራታቸውን ተናግረዋል።
ከፊታችን በመስከረም ወራት ለሚከበሩ ዘመን መለወጫና መሠል በዓላት አቅመ ደካሞች እንዳይቸገሩ የአካባቢው አመራር ህብረተሰቡን በማስተባበር ወገኖቻችን በዓሉን ደስተኛ ሆነው እንዲያሳልፉ ማገዝ ይገባል ሲሉም አቶ መኮንን አሳስበዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ናትናኤል ሚሊዮን በርክክብ ወቅት እንደተናገሩት፤ የብልጽግና ፓርቲ ሰው ተኮር ከሆኑ ተግባራት መከከል አንዱ አቅመ ደካሞች የሚታገዙበት ተግባር ነው ብለዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ማዕድንና ኢነርጂ ኤጄንሲና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አመራሮችና ባለሙያዎች ተጠናቆ ርክክብ የተደረገው የወይዘሮ አዳነች መኖሪያ ቤት፥ በክረምት በጎ ፈቃድ በክልሉ የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች የተሳተፉበት መሆኑንም ገልፀዋል።
የበጎ ፈቃድ ተግባር የአንድ ወቅት ብቻ ሳይሆን የሁልጊዜ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ አቶ ናትናኤል መክረዋል።
የቤቱ ግንባታ በአጭር ጊዜ መጠናቀቁን አቶ ናትናኤል ገልፀው፣ ይህም የአመራሩንና የባለሙያዎችን ቅንጅት በግልፅ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የጎምቦራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም ጎበና በበኩላቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ማዕድንና ኢነርጂ ኤጄንሲና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ሰው ተኮር ስራ በተግባር በመከናወናቸው ሊመሰገኑ እንደሚገባቸው አመላክተዋል።
ተግባሩ እጅግ አስቸጋሪ ህይወት ውስጥ ያሉ ሰዎችን ተደራሽ እያደረገ ያለ ስራ በመሆኑ መደጋገፍ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ተግባር ነው ሲሉም አቶ አብርሃም ተናግረዋል።
ቤት የተገነባላቸው ወይዘሮ አዳነች ሀፌቦ፣ ከዚህ ቀደም በክረምት ወቅት ጎርፍ ወደ ቤታቸው እየገባና ዝናብ እየዘነበ እንደሚቸገሩና አጋዥ የሌላቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ማዕድንና ኢነርጂ ኤጄንሲና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አመራሮችና ሠራተኞች የገነቡላቸው ቤት ይህን ችግር እንደሚቀርፍላቸው እልልታ በተሞላ አንደበታቸው ገልፀዋል።
የተደረገላቸው መልካም ተግባር የመኖር ተስፋቸውን እንዳለመለመላቸው ጠቁመው ፣ ይህን በጎ ተግባር ላደረጉላቸው አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
ተግባራቱ “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አካል መሆኑም ተገልጿል።
ዘጋቢ: በየነ ሰላሙ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
የልማት መጓተትን ለማስቀረትና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በህብረት ተደጋግፎ መሥራት እንደሚገባ ተገለጸ
ከፋፋይ ከሆኑ አጀንዳዎች በመራቅ ህብረታችንን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጳጉሜ 4 “የኅብር ቀን” ለአዲሱ ዓመት ለአቅመ ደካሞች የማዕድ ማጋራት አደረጉ