ሀዋሳ፡ ጳጉሜ 04/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የ2019 ዘመን መለወጫና የመስቀል በአል በሰላማዊ መንገድ እንዲከበር የፀጥታ ሀይሉ በመቀናጀት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የአርባምንጭ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ፡፡
የአርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ከከተማው ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ጋር በመቀናጀት ወንጀልን አስቀድሞ በመከላከሉ ረገድ ለፀጥታ ሀይሉ ስልጠና ሰጥቷል።
የአርባ ምንጭ ከተማ ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ሀላፊ ወ/ሮ ወይንሸት ሳሙኤል ከፊታችን የሚከበረው የዘመን መለወጫና የመስቀል በአል በሰላማዊ መንገድ እንዲከበር የፀጥታ ሀይሉ በመቀናጀት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አስታውቀዋል።
የአርባ ምንጭ ከተማ የቱሪዝም መዳረሻ በመሆኗ በርካታ እንግዶች ወደ ከተማዋ የሚመጡበት እድል ስላለ፥ ሰላሟ የተጠበቀ እና ዜጎች ያለስጋት በማንኛውም ሰዓት እንቅስቃሴ ማድረግ እንዲችሉ የከተማው ፖሊስ ከፀጥታ ሀይሉ ጋር በቁርኝት የሚሰራው ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።
በከተማው በተገነቡ መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት የሚያደርሱና በመንገድ ዳር የሚደረጉ ግብይቶችንም በእኔነት መንፈስ መቆጣጠር ያስፈልጋል ብለዋል ኃላፊዋ።
የአርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ክበበው አዳል የአርባ ምንጭ ከተማ ሰላሟ የተረጋገጠ ለነዋሪዎቿ ምቹና ለቱሪዝም ዘርፉ ተመራጭ መሆኗን ገልፀው ይህንን ሰላም ለማደፍረስና የስጋት ቀጠና እንድትሆን የሚፈልጉ ፀረ ሰላም ሀይሎችን መመከት የሚቻለው ያደግንበትን እሴት በመከተል የፀጥታ ሀይሉ በትኩረት መሥራት ሲችል ነው ብለዋል።
በበአላት ወቅት የትራፊክ አደጋ፣ የእሳት እና መሰል አደጋዎች እንዳይከሰቱ ህ/ሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግና የፀጥታ ሀይሉም የቁጥጥር ስራውን በቅንጅት መስራት እንዳለበት አስታውቀዋል።
በበአል ወቅት የማጭበርበር ወንጀል እና የሞባይል ስልክ ስርቆት እንዳይከሰት በሚደረገው ጥረት ፀጉረ ለውጥ ሰዎችን መረጃ ማጥራት እንደሚገባ ገልፀው፥ በበአል ግብይት ወቅት ባእድ ነገሮች ከምግብ ጋር ቀላቅሎ መሸጥና ሀሰተኛ የብር ኖት እንቅስቃሴ ሊኖር ስለሚችል የፀጥታ ሀይሉ በቅንጅት መስራትና ህ/ሰቡን ከአአጭበርባሪዎች መጠበቅ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
አካባቢው ሰላማዊ መሆኑ ያልተመቻቸው አጥፊዎች በሀሰተኛ ማህበራዊ ሚዲያ ሀሰተኛ መረጃዎችን ማሰራጨትና የብሔርና የሀይማኖት ግጭት ለመቀስቀስ የሚጥሩ ሀይሎችን መከታተልና ፖሊስ መረጃዎችን አጣርቶ ርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል።
የፀጥታ ሀይሉ ወንጀልን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸም ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ገልፀው፥ ፖሊስ ከሰላምና ፀጥታ መምሪያው ጋር ጠንካራ የመረጃ ልውውጥ በማድረግ እንደሚሰራ ነው ኮማንደር ክበበው የገለፁት።
የፀጥታ አካላትም ተልእኮን ሙያዊ ስነ ምግባራቸውን ጠብቀው በአግባቡ ለመተግበር ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ: ገነት መኮንን – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን

More Stories
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ከዓለም ባንክ የኦፕሬሽንስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ
አካል ጉዳተኝነት ውጤታማ ከመሆን ያልገደባቸው አቶ ሀብታሙ ለማ
የፈተና አስተዳደር ሥርዓትን በማዘመን ኩረጃን በማስቀረት የተሻሉ ተማሪዎችን ማፍራት እየተቻለ እንደሚገኝ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ገለጹ