በዓላትን ምክንያት በማድረግ በሚፈጸሙ የእንስሳት እርድ ለቆዳና ሌጦ ተገቢዉን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ ጳጉሜ 04/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የዘመን መለወጫና የመስቀል በዓላትን ምክንያት በማድረግ በሚፈጸሙ የእንስሳት እርድ ለቆዳና ሌጦ ተገቢዉን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

የሀድያ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ በ2019 በጀት ዓመት ከ88 ሺህ በላይ ቆዳና ሌጦ ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ መታቀዱን ገልጿል።

የሀድያ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ሀንቅሲዶ ገብሬ እንዳሉት ቆዳና ሌጦ ለሀገር ኢኮኖሚ ካላው ፋይዳ አንፃር እንደ ዞንም ለዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል።

በ2018 በጀት ዓመት 115 ሺህ ቆዳና ሌጦ ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለመላክ ታቅዶ 70 ከመቶ ማሳከት መቻሉንም ጠቅሰዋል።

በባለፉት ጊዜያት የቆዳና ሌጦ ዋጋ መቀነስ ሁኔታዎች መኖሩን ገልጸው፥ በዞኑ ህጋዊ ፈቃድ ያላቸው 11 ነጋዴዎች በዘርፉ በስፋት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

በ2019 በጀት ዓመት ባለፈው ዓመት የታዩ ጠንካራ ጎኖችን ይበልጥ በማጠናከር እና ድክመቶችን በማረም ከ88 ሺህ በላይ ቆዳና ሌጦ ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተለይ በመስከረም ወራት የሚከበሩ የእንቁጣጣሽ፣ “ያሆዴ” የሀድያ ብሔር ዘመን መለወጫ እና የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ በሚደረገው የእንስሳት እርድ ህብረተሰቡ ለቆዳና ሌጦ ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባም አቶ ሀንቅሲዶ አሳስበዋል።

በዘርፉ የተሰማሩ ነጋዴዎች በበኩላቸው ቆዳና ሌጦ የሀገር ሀብት መሆኑን በመገንዘብ ህብረተሰቡ በእርድ ወቅት ተገቢዉን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ በመጨረሻም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ለ2019 አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።

ዘጋቢ: ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና ጣቢያችን