ከፊታችን ለሚከበረው ለዘመን መለወጫ በዓል የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰትና ህጋዊ የንግድ ስርዓት እንዲሰፍን እየተሠራ መሆኑን የዲላ ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ አስታወቀ
ሀዋሳ: ጷግሜ 03/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከፊታችን ለሚከበረው ለዘመን መለወጫ በዓል የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰትና ህጋዊ የንግድ ስርዓት እንዲሰፍን እየተሠራ መሆኑን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የዲላ ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ አስታውቋል።
በምርት አቅርቦት ላይ እጥረት እና የጥራት ችግር እንዳይከሰት ለማድረግ ሰፊ የክትትል ሥራ እየተሠራ መሆኑም ተመላክቷል።
የበዓል ገበያ ከሌላ ጊዜ ይልቅ ሰፊ የግብይት ሂደት የሚከናወንበት በመሆኑ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ምክንያቶች ተቀዛቅዞ የነበረው የሰንበት ገበያ ማመቻቸታቸውን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የዲላ ከተማ አስተዳደር ንግድ እና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ኃላፊ ተወካይ አቶ ዳዊት አራርሶ ተናግረዋል።
አክለውም የረጅም ጊዜ የከተማው ማህበረሰብ ችግር ሆኖ የቆየውን የቁም እንስሳት ገበያ ለማቋቋም ከከተማው ማዘጋጃ ቤት ጋር በመቀናጀት ቦታ ማዘጋጀታቸውን እና ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ ወደ ሥራ በማስገባት ከህዝብ ተጠቃሚነት ባሻገር መንግስት ማግኘት ያለበትን የቀረጥ ገቢ እንዲያገኝ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በነበረው በአቅርቦት ችግር ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የፍጆታ ምርት አሁን ላይ በዓልን በማስመልከት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በተሠራው ሥራ የስኳር እና የዘይት ምርት ለሰንበት ገበያ ለማቅረብ እና ለመንግሥት ሠራተኞች ለማከፋፈል የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን ተናግረዋል።
ጂናድ ከተሰኘ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓት ልማት ድርጅት 40 ሺህ ሊትር ዘይት እና 1 መቶ 20 ኩንታል ስኳር ተዘጋጅቶ ለገበያ መቅረቡን ጠቁመው፤ በሌሎች ህብረት ሥራ ማህበራት ደግሞ 18 ሺህ ሊትር ዘይት እና 100 ኩንታል ስኳር ለገበያ እንዲቀርብ ስምምነት በመፈጸም ለህብረተሰቡ የማቅረብ ሥራ መጀመሩን አስረድተዋል።
አክለውም ከፊታችን ለሚከበረው ለዘመን መለወጫ በዓል የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰትና ህጋዊ የንግድ ስርዓት እንዲሰፍን እየተሠራ መሆኑን በመጠቆም ሸማቾች የተለያዩ የፍጆታ ዕቃ በሚሸምቱበት ጊዜ ህገ-ወጥ የዋጋ ጭማሪ እና ጊዜ ያለፈባቸውን ምርት ሲያጋጥማቸው ጥቆማ በመስጠት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓት ልማት ድርጅት የዲላ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ወዳጆ በበኩላቸው፤ ድርጅቱ በቂ የዘይት እና የስኳር ምርት በማቅረብ በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ደሳለኝ አብርሃም እና ወ/ሮ ሳምራዊት አያነው የአትክልት ነጋዴዎች ሲሆኑ፤ ለበዓሉ በቂ የፍጆታ ዕቃ በማቅረብ በተመጣጣኝ ዋጋ እየሸጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ያነጋገርናቸው የዲላ ከተማ ሸማቾችም የዶሮ ዋጋ ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ቅናሽ ማሳየቱንና ሌሎችም የፍጆታ ዕቃዎች ከመደበኛ ገበያም ሆነ ከሰንበት ገበያ ከወትሮ በተሻለ ሁኔታ በቅናሽ ዋጋ እየሸመቱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ: እንግዳየሁ ቆሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
“የፅናት ቀን” በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እየተከበረ ነው
ከአንድ ነጥብ አምስት ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የጉራጌ ዞን አስተዳደር ህንፃ እየተመረቀ ነው
በማህበራት ተደራጅተው ወደ ስራ የገቡ ወጣቶች ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን እያስመዘገቡ መሆኑ ተገለጸ