በማህበራት ተደራጅተው ወደ ስራ የገቡ ወጣቶች ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን እያስመዘገቡ መሆኑ ተገለጸ

በማህበራት ተደራጅተው ወደ ስራ የገቡ ወጣቶች ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን እያስመዘገቡ መሆኑ ተገለጸ


በከምባታ ዞን በዶዮገና ወረዳ በማህበራት ተደራጅተው ወደ ስራ የገቡ ወጣቶች ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን እያስመዘገቡ መሆናቸውን ገለጹ።


የወረዳው ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽሕፈት ቤት በበኩሉ፤ በበጀት ዓመቱ 173 ማህበራትን ወደ ስራ ማስገባቱን አስታውቋል።


”ሰላም ቅይጥ ግብርና ማህበር” የተሰኘ ማህበር ሰብሳቢ የሆኑት ወ/ሮ አባይነሽ አባቦራ፤ በውበት፣ በፍራፍሬና ሀገር በቀል ችግኝ በማፍላት እንዲሁም በንብ ማነብ ስራ ላይ 30 አባላት ተደራጅተው ለሌሎችም የስራ ዕድል ፈጥረው እየሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል።


”በአደይ ፕሮግራም” ድጋፍ 30 ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችን ማግኘታቸውን ጠቁመው፤ 5 ዓመታትን የዘለቀው ይህ ማህበር የብድር አቅርቦት በባለድርሻ አካላት ተመቻችቶለት በትጋት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


በሌላ በኩል በ”ፍቅር ማህበር” በጓሮ አትክልት ልማት ስራ ከተሰማሩ ወጣቶች አንዱ የሆነው ወጣት አዲሴ ቦቄ፤ በዓመት ሦስት ጊዜ በማምረት እስከ አንድ ሚሊየን ብር ገቢ ማግኘት መቻላቸውን ገልጿል።


በማህበሩ ራስን ከመቻል አልፈው ለ12 ወጣቶች የስራ ዕድል እንደፈጠሩ የሚናገረው ወጣቱ፣ እያጋጠማቸው ያለው የመሬት እጥረት እንዲቀረፍላቸው፣ የግብዓት እንዲሁም የገበያ ትስስርም እንዲፈጠርላቸው ጠይቋል።


በተመሳሳይ በዶሮ እርባታ ዘርፍ የተሰማራው ”ፅናት” የዶሮ እርባታ ማህበር 15 አባላትን በአንድነት አቅፎ 500 እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን በማርባት እንደሚሰራ የማህበሩ አባል ወ/ሮ ሳራ አረጋ ጠቅሰዋል።


በአደይ ፕሮግራም ስልጠና እንዳገኙ የሚገልጹልን ወ/ሮ ሳራ፣ ከድርጅቱም 500 ጫጩቶችን እና 27 ኩንታል መኖ በድጋፍ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።


ይሁን እንጂ ስራውን ይበልጥ ለማስፋፋት የቦታ እጥረት ከፍተኛ ፈተና እንደሆነባቸው ተናግረውው፣ የሚመለከተው አካል አስፈላጊውን የቦታ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።


የዶዮገና ወረዳ ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደገፈ አኔቦ ለጣቢያችን እንደገለጹት፤ በወረዳው የሚገኙ ስራ አጥ ወጣቶችን በመለየት በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በአገልግሎት ዘርፎች እንዲደራጁ ተደርጓል።


በዚህም በሦስቱም ዘርፎች 173 ማህበራትን በማደራጀት ወደ ስራ ማስገባት ተችሏል ብለዋል።


በስራ እድል ፈጠራው ላይ በተለይም ከስደት ተመላሽ ለሆኑ ዜጎች እና ለተፈናቃዮች ቅድሚያ መሰጠቱን የገለጹት ኃላፊው፤ ከዚህ በተጨማሪም በህጋዊ መንገድ የውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት የመፍጠር ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።


የመንግስትን ጥረት ለማገዝ “አደይ ፕሮግራም” ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ያነሱት አቶ ደገፈ፤ ፕሮግራሙ ለ3 ሺህ 800 ወጣቶች የስራ ስልጠና ከመስጠት ጀምሮ የ6 ሚሊዮን 2 መቶ ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን አብራርተዋል።


ጽህፈት ቤቱ አዳዲስ ማህበራትን ከመደገፍ ባለፈ፣ ቀደም ሲል በራሳቸው ተነሳሽነት የተደራጁ ማህበራትን ሙያዊ ድጋፍና ክትትል የማድረግ ስራውን አጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቋል።


ከቦታ እጥረት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት የትምህርት ቤቶችን መሬት ጨምሮ ሌሎች ሊለሙ የሚችሉ መሬቶችን የማመቻቸት ስራ እየተሰራ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል።

መሬት ወስደው በአግባቡ ስራ ላይ ካላዋሉ ማህበራት ላይ መሬቱን በመውሰድ፣ በትጋት ለሚያለሙ ማህበራት አሳልፎ ለመስጠት ቁርጠኛ አቅጣጫ መቀመጡንም አስገንዝበዋል።


ጽህፈት ቤቱ በቀጣይ ከገበያ ትስስር ጋር በተያያዘ የሚታዩ ድክመቶችን በማረም በትኩረት እንደሚሰራ ኃላፊው አመልክተዋል።


ዘጋቢ: ኤደን ተረፈ – ከሆሳዕና ጣቢያችን