በካራት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በመንግሥትና በአጋር ድርጅቶች በጋራ ጥረት የተገነቡ ፕሮጀክቶች ተመረቁ

በካራት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በመንግሥትና በአጋር ድርጅቶች በጋራ ጥረት የተገነቡ ፕሮጀክቶች ተመረቁ

በመንግሥት፣ በአጋር ድርጅቶች እና በማህበረሰብ ተሳትፎ በላቀ ቅንጅት የተገነቡ ዘርፈ ብዙ የሆስፒታል መሰረተ ልማት እና የአገልግሎት ማሻሻያ ፕሮጀክቶች በዛሬው ዕለት ተመርቀው ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት ሆኑ።

ከተገነቡትና እድሳት ከተደረገላቸው መካከል ምቹ ክሊኒክ፣ የእናቶችና ህፃናት ጤና አገልግሎት፣ ድንገተኛ ህክምና፣ የአንድ መስኮት አገልግሎት ማዕከል፣ የእናቶች ማረፊያ ግንባታን ጨምሮ ሌሎች ማስፋፊያ ይገኙበታል።

እነዚህ አገልግሎቶች ከ1 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ፈጣንና ጥራት ያለውን የህክምና አገልግሎት ለመስጠት አቅም እንደምፈጥሩ ተገልጿል።

የምረቃ መርሃ ግብሩ በሀገር ሽማግሌዎች ምርቃት እና የባህል ሽማግሌዎች ምርቃት የተከፈተ ሲሆን፤ የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ገላነህ ኩሴ ለተዘጋጁት እንግዶች፣ የአጋር ድርጅት ተወካዮች እና የአካባቢው ነዋሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኃላፊው በመልዕክታቸው የፕሮጀክቱ መሳካት የሁሉንም አካላት ቅንጅት የሚጠይቅ እንደነበር ገልጸው ለተደረገው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የሥነ ተዋልዶ ጤናና መብቶች ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ድላየሁ በቀለ ስለ አዲሱና ምቹ ክሊኒክ ሰፊ ገለፃ አድርገዋል።

የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር የሥነ-ተዋልዶ፣ የቤተሰብ ዕቅድ እና የአፍላ ወጣቶችና የወጣቶች ጤና ቡድን መሪ አቶ ሞቱማ በቀለ ባደረጉት ንግግር የማስፋፊያው መከፈት የእናቶችን እና የህፃናትን ሞት ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት የሚያጠናክር መሆኑን ጠቁመዋል።

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የተጋበዙት ሙሉቀን ተስፋዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው ክሊኒኩ በተለይም እናቶች ምቹና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት እንዲያገኙ ታስቦ የተገነባ ነው ብለዋል።

የኢፌዴሪ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ መስፍን ሙሉነህ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከማህበረሰቡ እና ከመንግሥት ጋር ተቀናጅተው መስራታቸው ለወሳኝ የልማት ግቦች መሳካት ያለውን አዎንታዊ ሚና አጉልተው አሳይተዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ እና የሆስፒታሉ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ገለቦ ጎልቶሞ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የመንግሥት በጀት ብቻውን ሁሉንም የልማት ፍላጎቶች ማሟላት በማይችልበት በአሁኑ ወቅት፥ መሰል የሦስትዮሽ ቅንጅቶች ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አክለውም “ይህ ፕሮጀክት ሕዝባችን፣ መንግሥት እና የልማት አጋሮቻችን በአንድ ዓላማ ስር ሲሰባሰቡ ምን ያህል ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ያሳየ ሁነኛ ማረጋገጫ ነው” ብለዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ በክልሉ ያለውን የጤና ሽፋንና ጥራት ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው፣ የተገነቡትን አዳዲስ መሰረተ ልማቶችና ምቹ ክሊኒክ በአግባቡ በመጠበቅና የሰው ኃይል አቅምን በማሳደግ ህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ እንደሚደረግ አመላክተዋል።

በዕለቱ በግንባታውና በቁሳቁስ ድጋፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አጋር ድርጅቶችና የህብረተሰብ ተወካዮች የባለቤትነትና የምስጋና ሰርተፊኬት የተሰጠ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ ለህብረተሰቡ ፈጣንና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆኑ ተገልጿል።

ዘጋቢ: ተዋበች ዳዲ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን