የሀገርን ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥና ለመገንባት የትውልዱን አእምሮ አስቀድሞ መቅረጽ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ጳጉሜን 02/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) “ለምናልማት ሀገር፤ ትውልድ ቀራጩ መምህር” በሚል መሪ ቃል የኮሬ ዞን የኬሌ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽሕፈት ቤት ከመምህራን ጋር ያካሄደው የምክክር መድረክ በኬሌ ከተማ ተጠናቋል።
በመድረኩ ላይ ሀገርን የማልማትና የመገንባት ትልቁ መሠረት ብቁና የታነፀ ትውልድ ማፍራት እንደሆነ የተመላከተ ሲሆን፤ ለዚህ ደግሞ ትውልድ ቀራጭ ለሆኑ መምህራን ተገቢውን ትኩረት መስጠትና አቅማቸውን ማልማት እንደሚገባ ተመላክቷል።
የኬሌ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኤዴማ ጭርጋ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “ሀገር ለማልማት አእምሮው የበለፀገ ትውልድ መገንባት ቅድመ-ሁኔታ ነው” ብለዋል።
አዲሱ የትምህርት ዘመን ተጀምሮ የመማር-ማስተማሩ ሂደት ከመጀመሩ አስቀድሞ ከመምህራን ጋር እንዲህ ዓይነቱን የጋራ ውይይት ማድረግ ማስፈለጉንም አስረድተዋል።
ኃላፊው አክለውም፤ ያለ መምህራን ንቁ ተሳትፎ የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግቦች ስኬት ሊታሰብ እንደማይችል ገልጸው፤ መምህራን ጥያቄዎችንና ቅሬታዎችን ከማንሳት ባሻገር ለሚነሱ ችግሮች ሁልጊዜም የመፍትሔ አካል በመሆን የነቃ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የኬሌ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ተማሙ ጀማል በበኩላቸው፤ በዕውቀትና በሥነ-ምግባር የታነፀ ዜጋ ሳይፈጠር ሁለገብ ሀገራዊ እድገት እውን ሊሆን እንደማይችል አስገንዝበዋል።
በመሆኑም ለትምህርት ጥራት መሻሻልና ለነገዋ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ግንባታ መምህራን የተጣለባቸውን ከፍተኛ ሙያዊና ሀገራዊ ኃላፊነት በብቃት እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ከንቲባው ከመምህራን በኩል የተነሱትን ቅሬታዎች በተመለከተ በሰጡት ምላሽ፤ ከደረጃ እድገት መዘገየት፣ ከትምህርት ግብዓቶች እጥረትና የወር ደመወዝ በወቅቱ ካለመከፈል ጋር ተያይዘው ለቀረቡ ጥያቄዎች እልባት ለመስጠት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
በውይይቱ ላይ ከተሳተፉ መምህራን መካከል መምህር ታገል ታዘዘና መምህርት ደብሪቱ ደበበ በሰጡት አስተያየት፤ ከዚህ ቀደም መሰል መድረኮች በአመራሮች ብቻ ይከናወኑ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ግን የሙያው ባለቤት ከሆኑት መምህራን ጋር በቀጥታ መደረጉ መድረኩን የተለየና ውጤታማ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
ተሳታፊ መምህራኑ አክለውም፤ ያለ መምህር ተማሪም ሆነ ትምህርት የለም ያሉ ሲሆን፤ ብቁ ትውልድ ለመቅረጽ ደግሞ አስቀድሞ መምህሩን ማልማትና መደገፍ እንደሚገባ አስምረውበታል።
በመሆኑም በመንግሥት በኩል የደረጃ እድገት አፈጻጸም መዘገየት፣ የትምህርት ቁሳቁስ እጥረትና የደመወዝ ክፍያ መዘግየት ችግሮች በፍጥነት እልባት እንዲያገኙ ጠይቀዋል።
ዘጋቢ: ምርጫ መላኩ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
የብደርና ቁጠባ ህብረት ስራ ማህበራት የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮችን ላይ የሚያደርጉት አበረታች ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተገለጸ
በኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ውስጥ ጀምሮ ግማሽ ክፍለ ዘመን የሚጠጋ ዓመታትን በቤዝ ጊታር የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋችነት ያሳለፉት አንጋፋው ሙዚቀኛ ተፈራ ሸንቁጤ
ባህልና ስፖርትን ለማልማት፣ ለመጠበቅና ለማስተዋወቅ ማህበራዊ መሠረት መያዝ እንዳለበት ተገለጸ