በተፈጠረላቸው የስራ እድል ተጠቃሚ በመሆናቸው መደሰታቸውን ወጣቶች ተናገሩ

ሀዋሳ፡ ጳጉሜን 02/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በተፈጠረላቸው የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን በቦረዳ ወረዳ በድንጋይ ከሰል ምርት ስራ ዘርፎች የተሰማሩ ወጣቶች ተናገሩ፡፡

የወረዳው ስራና ክህሎት ጽ/ቤት በበኩሉ የወረዳውን ወጣቶች ተጠቃሚነት ለማሳደግ በመንግስትና አጋር ጅርጅቶች ድጋፍ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

ከኮዶ ማይኒንግ ኮሚሽን ስራ ማህበር ወጣት ዳዊት ማሞ እና ከትጋት ማህበር ወጣት ትዕግስት አሻ በቦረዳ ወረዳ በተለያዩ ስራ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው በመስራት ውጤታማ መሆን መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ወጣቶቹ አክለውም ከሚያገኙት ገንዘብ ጥሪት ለማፍራት 40 ከመቶ እየተጠቀሙ 60 ከመቶውን በአግባቡ እየቆጠቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሌሎች በድንጋይ ከሰል ማዕድን ስፍራ ላይ የተሰማሩት ወጣት ካሳሁን ከተማ እና ወጣት ዝናሽ አለማየሁ በበኩላቸው ትምህርት ጨርሰው ቦታ ያላገኙ በርካታ ስራ አጥ ወጣቶች በመሠባሰብ ወደ ስራ መግባታቸውንና ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን የሚናገሩት ወጣቶቹ ከወረዳው ስራና ክህሎት ጽ/ቤት ድጋፋዊ ክትትል እንደሚያደርጉላቸውና በቀጣይም የተሻለ ደረጃ ለመድረስ ጠንክረው እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የወረዳው ስራና ክህሎት ጽ/ቤት ሀላፊ ተወካይ አቶ ስምዖን ኃይሌ እንደወረዳ በመንግስትና በአጋር ድርጅቶች ድጋፍ ወጣቶች የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መሠራቱን ተናግረዋል።

በማዕድን ስፍራ በተፈጠረው ስራ እድል በ 24 ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበራት ውስጥ በሶስት የስራ ዘርፎች 5780 ወጣቶች ተሰማርተው ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

ወጣቶቹን ወደ ስራ ከማሰማራት ባለፈ የስብዕና ግንባታ ስልጠና በየጊዜው እየተሰጠ መሆኑንና በየሳምንቱ ከሚያገኙት ገንዘብ ከአርባ ስልሳ እየቆጠቡ መሆናቸውንም አቶ ስምዖን ተናግረዋል።

ዘጋቢ: ማርታ ሙሉጌታ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን