በኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ውስጥ ጀምሮ ግማሽ ክፍለ ዘመን የሚጠጋ ዓመታትን በቤዝ ጊታር የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋችነት ያሳለፉት አንጋፋው ሙዚቀኛ ተፈራ ሸንቁጤ
ሰሞኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለኪነጥበብ ባለሙያዎች ከነሐሴ 23/2018 ዓ.ም ጀምሮ ለ10 ተከታታይ ቀናት የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰጥቶ ነበር።
እኛም በስልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ በተገኘንበት አጋጣሚ ከአንጋፋው የቤዝ ጊታር የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋች ተፈራ ሽንቁጤ ጋር ቆይታ አድርገናል።
የዛሬው አንጋፋው የቤዝ ጊታር ተጫዋቹ ተፈራ ሸንቁጤ ገና በልጅነት ዕድሜያቸው ነበር ባህላዊ የክራር መሳሪያ ጨዋታ ፍቅር ያደረበት፤ በልጅነታቸውም ወደዚሁ ሙያ በመግባት ህይወታቸውን ሙሉ ሰጥተው ሀገራቸውን ማገልገል ጀመሩ።
በ 17 ዓመታቸው ነበር በወቅቱ በነበረው የጦር ሰራዊት የባህል ኪነት ቡድን የተቀላቀሉት።
በልጅነት ዕድሜያቸው የሚጫወቱትን ባህላዊ የክራር መሳሪያቸውን በመያዝ በክፍለ ጦሩ በተደራጀው የኪነት ባንድ ቡድን አባል መሆን የቻሉት።
የመጀመሪያ ስራቸውንም በቀድሞው ኤርትራ ክፍለ ሀገር በአስመራ የሙዚቃ ስራቸውን አንድ ብለው ጀመሩ።
አንጋፋው ባለሙያ በጦር ሰራዊት ውስጥ እንዲቀላቀሉ በአርያነት የሚጠቀሱት ዘመን ተሻጋሪዎቹ እንደ ሻምበል ደጀኑ ሽፈራው እና ሌሎች ባልደረቦቻቸው አቶ ተፈራ ዛሬ ላይ ጠንካራ እና ብርቱ እንዲሆኑ መሠረት እንደሆኑአቸው ይናገራሉ።
በወጣትነት ዘመናቸው እንደነበረው ለስራቸው ያላቸው ፍቅር ዛሬም አልቀዘቀዘም፤ የተሰጣቸውን ተግባር ብስለት በተሞላበት መንገድ የሙያ ስነምግባርን ተላብሰው ይፈፅማሉ።
ከጦር ሰራዊት የባህል ኪነት ቡድን ከወጡ በኋላም በተለያዩ ህዝባዊ እና መዝናኛ ስፍራዎች ላይ ከሙያ ባልደረቦቻቸው ጋር የጥበብ ስራዎቻቸውን በማቅረብ ረጅም አመታትን አገልግለዋል።
አቶ ተፈራ ሸንቁጤ በቀድሞው የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የባህል ኪነት ቡድን አባል ከሆኑበት ጊዜ አንስተው የብሔር ብሔረሰቦች ቱባ ባህልና እሴቶች ለዓለም ጎልቶ እንዲወጣና እንዲተዋወቅ ጥበብ በሰጠቻቸው ሙያ ለ15 አመታት በኪነት ቡድኑ በአባልነት አገልግለዋል።
በዚህ ሙያቸውም ከሀገር ውጪ ሄደው የጥበብ ስራቸውን ማቅረብ ችለዋል።
የቀድሞ የደቡብ ክልል እንደ አዲስ ከተደራጀ በኋላም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የባህል ኪነት ቡድንን በመቀላቀል በቤዝ ጊታር ተጫዋችነት እያገለገሉ ይገኛሉ።
ግማሽ ክፍለ ዘመን የሚጠጋ ዓመታትን የተሸጋገረው አንጋፋው የቤዝ ጊታር የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋች አቶ ተፈራ ሸንቁጤ ወርቃማ የስራ ዓመታትን የሙያ ስነምግባር ተላብሰው ዛሬም ድረስ ለሌሎች አርአያ በመሆን የተጣለባቸውን ሃላፊነት በብቃት እየተወጡ ይገኛሉ።
የሙዚቃ ሙያተኛ ብዙውን ጊዜ በዓላትን ከቤተሰብ ጋር አያሳልፍም ያሉት አቶ ተፈራ፤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በሚፈጠሩ መድረኮች ላይ በመገኘት ሰዎችን በማዝናናት እንደሚያሳልፍም ይገልጻሉ።
አቶ ተፈራ 64 ዓመታቸው ሲሆን ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ናቸው።
በዚህ በረጅም ዓመታት የጥበብ ጉዞ ውስጥ በርካታ ውጣ ውረዶችን በማለፍ በልጅነታቸው የተቀላቀሉበትን የሙዚቃ መሳሪያ እየተጫወቱ ይገኛሉ።
ከስራ ባልደረቦቻቸው ጋርም በአዲስ የስራ ሞራልና በየመድረኩ ታዳሚዎችን እያስደመሙ አይረሴ ትውስታ እየጣሉም ነው።
በኪነት ቡድን ቆይታቸውም የብሔረሰቦችን ባህልና ትውፊቶች በሙዚቃ መሳሪያ ታጅበው በዓለም አቀፍ ደረጃ ጎልተው እንዲታወቁ፣ የህዝቦችን አንድነት በማጠናከር የሀገርን ገፅታ የሚገነቡ ስራዎችን ጥበብ በሰጠቻቸው ሙያ በመጠቀም እስከ ዛሬም ከማገልገል አልተቆጠቡም።
የኪነት ቡድን ስራ ጥልቅ መናበብ፣ ትዕግስትና ጊዜ ሰጥቶ መዘጋጀት ይፈልጋል።
በቆይታቸውም በርካታ የሙዚቃ ሙያተኞችን በማብቃት ዛሬ በተሻለ ቦታ እንዲገኙ መሰረት ጥለዋል።
አሁንም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የባህል ኪነት ባንድ ውስጥ ለሙያው ፍቅር ያላቸውን ወጣቶች ልምዳቸውን እያካፈሉ መሆናቸውን ገልፀውልናል።
ሙዚቃ ታላቅ ጥበብ ነች፤ ያከበራትን የምታከብርም ነች የሚሉት የቤዝ ጊታር ተጫዋች፤ የሙዚቃ ህይወት ፅናትና ትግስት የሚፈልግ ረጅም ጊዜ ሰጥቶ መለማመድን የሚጠይቅ እነንደሆነ ጠቁመዋል።
በቀጣይ ዓመታትም የረጅም ጊዜ ልምዳቸውን በመጠቀም ተተኪዎችን ለማፍራት ዝግጁ መሆናቸውን ነግረውናል።
ዘጋቢ፡ ተዘራ በቀለ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
የብደርና ቁጠባ ህብረት ስራ ማህበራት የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮችን ላይ የሚያደርጉት አበረታች ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተገለጸ
የሀገርን ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥና ለመገንባት የትውልዱን አእምሮ አስቀድሞ መቅረጽ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ
ባህልና ስፖርትን ለማልማት፣ ለመጠበቅና ለማስተዋወቅ ማህበራዊ መሠረት መያዝ እንዳለበት ተገለጸ