የኢትዮጵያ «ቢጫ ወርቅ» ወደ ውድ የገቢ ምንጭነት የተቀየረው ሰም

የኢትዮጵያ «ቢጫ ወርቅ» ወደ ውድ የገቢ ምንጭነት የተቀየረው ሰም

ኢትዮጵያ በንብ ሀብቷና በማር ምርቷ ከአፍሪካ አህጉር በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀስ ሀገር ናት። ይሁን እንጂ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከእያንዳንዱ የንብ ቀፎ ውስጥ ከሚገኘው ማር ባልተናነሰ እጅግ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እሴት ያለው ሌላ የተፈጥሮ ሀብት ትኩረት ተነፍጎት ቆይቷል፤ እሱም ሰም ነው።

አብዛኞቹ የአገራችን ንብ አናቢዎች ሰምን እንደ አላስፈላጊ ቆሻሻ ይቆጥሩት ነበር። ለገበያ ለማቅረብ የሚወጣው ድካምና የሚገኘው አነስተኛ ዋጋ አይመጣጠንም በሚል ተስፋ በመቁረጥ፣ ማሩን ከተጠቀሙ በኋላ ሰሙን አውጥተው ይጥሉት ወይም ያቃጥሉት እንደነበር የሲቲጂኤን ዘገባ ያስረዳል።

በዘርፉ ላይ የተሰማሩት አርሶአደር አቶ ዋሲሁን ተመሰገን እንደሚያስረዱት ከሆነ፣ ቀደም ሲል የነበረው አመለካከትና የገበያ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል።

«ቀደም ሲል ሰም በጣም ርካሽ ስለነበረና ለገበያ ማቅረቡም ድካሙን የማይመጥን በመሆኑ ይጣል ነበር። አሁን ግን ከማር ያላነሰ ጥቅም እየሰጠን ይገኛል። በጥንቃቄ ሰብስበን ይዘን ለገበያ ምናቀርበው ሲሆን፣ በብዙ አጋጣሚዎች ከማር በላይ ገቢ እያስገኘልን ነው። ድሮ አንድ ኪሎ ሰም ከ200 እስከ 300 ብር ብቻ እንሸጥ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን እንደ ጥራቱ ደረጃ ከአክሲዮን እስከ 1,500 ብር እና ከዚያ በላይ እያወጣ ይገኛል» ብለዋል።

የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች መነቃቃትና የሰም ፍላጎት መጨመር ይህ የዋጋ ጭማሪና የገበያ መነቃቃት በዋናነት የተከሰተው በሀገር ውስጥ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እያደገ በመምጣቱ ነው። ቀደም ሲል የሚመረተው ጥቂት የሰም ምርት ለውጭ ገበያ (Export) ብቻ ይላክ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን በሀገር ውስጥ የሚሰሩ የሳሙና፣ የኮስሞቲክስ (የውበት እቃዎች) እና የመድኃኒት ማዘጋጃ ፋብሪካዎች ዋና ግብአታቸው አድርገውታል።

የሰም አዘጋጅና አቅራቢው አቶ ተስፋዬ ባዬ እንደሚያብራሩት፣ የሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች ፍላጎት አሁን በኢንዱስትሪ ደረጃ ማደጉ ዘርፉን ሙሉ በሙሉ ለውጦታል።

ያልተነካው አቅምና የ«የሌማት ትሩፋት» አዎንታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ ሲሆን፥ እንደ መረጃዎች ከሆነ ኢትዮጵያ በዓመት እስከ 5,000 ቶን ሰም የማምረት አቅም ያላት ቢሆንም፣ አሁንም ለአለም አቀፍ ገበያ የሚቀርበው እጅግ ጥቂቱ ነው። ይህን ያልተነካ ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት ይፋ የሆነው «የሌማት ትሩፋት» መርሃ ግብር ትልቅ ድርሻ እየተጫወተ ይገኛል።

ባለፉት ዓመታት በዚህ መርሃ ግብር አማካኝነት ባህላዊ የንብ ቀፎዎችን ወደ ዘመናዊ መቀየር መቻሉን የዘገበው ሲቲጂኤን፥ የንብ አናቢዎች ቁጥርና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንዲያድግ መደረጉን አመላክቷል።

የማርና የሰም ምርት አቅም ቀደም ሲል ከነበረበት በሁለት እጥፍ እንዲያድግ መንገድ መክፈቱን ያወሳው ዘገባው፥ በግብርና ሚኒስቴር የአማካሪነት ድርሻ ያላቸው ወይዘሮ ፅጌረዳ ፈቃዱ እንደገለፁት፣ ከባህላዊ ወደ ዘመናዊ የማነብ፣ የማራባት ስልት መሸጋገር ለምርት እድገት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፥ «ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያ የሚሆን ከፍተኛ የሰም ምርት እያመረትን እንገኛለን። ነገር ግን አቅማችን ከዚያ በላይ ነው። ቀፎዎችን ወደ ዘመናዊ ስንለውጥ የሰም ምርቱም አብሮ ይጨምራል። ምንም እንኳን ትኩረታችን በማር ላይ ቢሆንም፣ ለሰም ምርትም አሁናዊ ድጋፍ እያደረግን እንገኛለን» ሲሉ ገልፀዋል።

የግብርና ኢኮኖሚ ባለሙያዎችና የዘርፉ ተንታኞች እንደሚያመላክቱት፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሰም ገበያ ላይ ያላትን ድርሻ ለማሳደግ ገና ብዙ የሚቀራት ሥራ እንደለ ያመላከተው ዘገባው፥ የጥራት ደረጃን መጠበቅ የውጭ ሀገራት የኮስሞቲክስና የመድኃኒት ኩባንያዎች ኦርጋኒክና ከኬሚካል ነፃ የሆነ ሰም (Organic Beeswax) ይፈልጋሉ። የኢትዮጵያ ሰም ተፈጥሯዊነቱ የተጠበቀ በመሆኑ ከፍተኛ ተፈላጊነት አለው፤ ነገር ግን የማጣራትና የጥራት ደረጃን የማስጠበቅ ስራዎች ሊበለፅጉ እንደሚገባ አስረድተዋል።

ሰምን በጥሬው ከ መላክ ይልቅ በሀገር ውስጥ ደረጃ ተሰናድቶና ተዘጋጅቶ (Processed) ለውጭ ገበያ ቢቀርብ ሀገሪቱ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ በከፍተኛ ሁኔታ ያሳድገዋል የሚሉት ባለሙያዎቹ፥ አብዛኛው የሀገራችን አርሶአደር/ንብ አናቢ አሁንም ቢሆን የሰም ማጣራት ቴክኖሎጂ እጥረት አለበት። የግብርና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ለንብ አናቢው የሰም አሰባሰብና አጠባበቅ ስልጠናዎችን አጠናክረው ሊሰጡ እንደሚገባ ተመላክቷል።

በአጠቃላይ «ይጣል» የነበረው የንብ ሰም ዛሬ ላይ የብዙ አባወራዎችን ኑሮ የሚደግፍና የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችን የሚያንቀሳቅስ «ቢጫ ወርቅ» ሆኗል። የዘመናዊ ንብ ማራባት ቴክኖሎጂ መስፋፋትና የገበያ ትስስሩ እየጠነከረ የመጣበት መንገድ ከተቀናጀ፣ ኢትዮጵያ በማር ብቻ ሳይሆን በሰም ምርትም ቢሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ አቅሟን አውጥታ እንድትጠቀም ትልቅ እድል ይፈጥርላታል።

ዘጋቢ፡ ዘላለም ተስፋዬ