የአሪ ዞን በ2018 በጀት ዓመት ላስመዘገበው የገቢ አሰባሰብ ስኬት በክልል ደረጃ ዕውቅና ተቸረው

የአሪ ዞን በ2018 በጀት ዓመት ላስመዘገበው የገቢ አሰባሰብ ስኬት በክልል ደረጃ ዕውቅና ተቸረው

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአሪ ዞን ገቢዎች መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት የገቢ አሰባሰብ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ አካሄደ።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ እንደገለጹት፤ ዞኑ በ2018 በጀት ዓመት ባከናወነው የገቢ አሰባሰብ ሥራ በክልል ደረጃ ካሉት መዋቅሮች የተሻለ አፈፃፀም በማስመዝገብ የላቀ ዕውቅና ማግኘት ችሏል። ይህ ስኬት በዞኑ ከተከሰተው የማርበርግ በሽታ ጫና በመቋቋምና ከ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት በማጠናቀቅ ማግስት የተገኘ በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

ዋና አስተዳዳሪው አክለውም «የገቢ አሰባሰብ ሥራ የሕዝብና የሀገር ልማት መሠረት እንደመሆኑ መጠን ለአንድ ተቋም ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁሉም አካላት ቅንጅታዊ ጥረት ውጤት ነው» ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት በተከናወኑ የተቀናጁ ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን የጠቆሙት አቶ አብርሃም፣ በቀጣይም በየደረጃው ያለው የመንግሥት መዋቅር ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል።

የአሪ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ታደለች ምክሬ በበኩላቸው፤ የተገኘው ስኬት በክልል ደረጃ ከተደረገው ተከታታ ድጋፍና ክትትል ባሻገር፣ በዞን ደረጃ በየወሩ ጥብቅ የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ በማካሄድና እንደ ሁኔታው የአሠራር ስልቶችን በመቀየር የተገኘ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።

መምሪያ ኃላፊዋ አክለው እንዳሉት፤ በበጀት ዓመቱ ያጋጠሙ ክፍተቶችን በማረም እና የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋፋት፣ የዞኑን የገቢ አቅም አሟጦ ለመሰብሰብ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋቱን አመላክተዋል።

በዚህም መሠረት የዓመቱን ዕቅድ በ12 ወራት በመሸንሸን በ2019 በጀት ዓመት ከ1.7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ሙሉ ተግባር መገባቱን አረጋግጠዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የጋዘር ከተማ ከንቲባ አቶ በለጠ ማጎ እና የባካ ዳውላ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መሠረት በጋሌ፤ የተመዘገበው የላቀ አፈፃፀምና በክልል ደረጃ የተገኘው ዕውቅና የሕዝቡና የመላው አመራር የጋራ ጥረት ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።

አክለውም በቀጣይም ጥንካሬዎችን በማስቀጠል እና የታዩ ማነቆዎችን በማረም ለተያዘው የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ስኬት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ: ፍቃዱ ግዲ – ከጂንካ ጣቢያችን