የአንድን ሀገር እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ ትምህርትና ስልጠና ወሳኝ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ

የአንድን ሀገር እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ ትምህርትና ስልጠና ወሳኝ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ

‎ቢሮው ይህንን ያስታወቀው ዳይናሚክ ሆሪዞን ኮሌጅ በ2018 ትምህርት ዘመን በተለያዩ የትምህርት መስኮች ከአምስት መቶ በላይ ተማሪዎችን በዲግሪና በዲፕሎማ ባስመረቀበት ወቅት ነው።

‎ በመርሃ-ገብሩ የኮሌጁ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተመስገን ካሣ፤ ኮሌጁ በ2012 ዓ.ም እውቅና አግኝቶ የመማር ማስተማር ስራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በመደበኛ፣ በሳምንቱ መጨረሻ እና በርቀት መርሃ-ግብሮች በተለያዩ ዘርፎች በጥራት እያሰለጠነ መምጣቱን ተናግረዋል።

አክለውም የአንድን ሀገር እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ ትምህርትና ስልጠና ወሳኝ በመሆኑ በዚህ ኮሌጅ ዛሬ የተመረቃችሁ ሁሉ ሥራ በግል፣ በቤተሰብ እና በቡድን በመደራጀት የምትፈጥሩ እንደሆኑ እምነቴ ነው ብለዋል።

ተመራቂ ተማሪዎች ወደ ስራ ዓለም ከመግባታቸው በፊት አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮች ላይና ለስራ ዝግጁ እንዲሆኑ ከማድረግ አኳያ ብቁ አድርጎ ማውጣት ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

‎የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ሥራና ክህሎት ቢሮ ተወካይና የተቋማት አቅም ግንባታና ጥራት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደስታ ገቲሳ በበኩላቸው፤ ዳይናሚክ ሆሪይዞን ኮሌጅ ክህሎት መር ስልጠና ሀገራዊ ለውጥን የሚያስቀጥል በመሆኑ ተመራቂዎች የተፈጠረላቸውን ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም ራሳቸውን ለስራ ፈጠራ ማዘጋጀት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

‎ኢትዮጵያ የሪፎርም ሥራዎችን በየዘርፉ እያካሄደች እንደሚትገኝና በርካታ ድሎች እየተመዘገቡ ይገኛል ብለዋል።

‎በምረቃ ስነ-ሥርዓቱ አግኝተን ያነጋገርናቸውን ተመራቂዎችና የተመራቂ ቤተሰቦች በሰጡት አስተያየት፤ የኮሌጁ መቋቋም የአካባቢው ማህበረሰብ ተማሪዎች ትምህርት ፍለጋ ርቀት ተጉዘው ከአላስፈላጊ ወጪና እንግልት ታድጓል ሲል ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ አሸናፊ ግዛው – ከዋካ ጣቢያችን