ሚካኤል አርቴታ ለአርሰናል 250ኛ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታቸውን ሊመሩ ነው
የአርሰናሉ አሰልጣኝ ሚካኤል አርቴታ የፊታችን ሰኞ ከአስቶንቪላ ጋር በሚያደርጉት ፍልሚያ በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ ውስጥ ስማቸውን በደማቁ የሚያጽፍ ሌላ አዲስ ምዕራፍ ይከፍታሉ።
በቪላ ፓርክ በሚደረገው በዚህ ጨዋታ የባስኩ ተወላጅ አሰልጣኝ በአንድ ክለብ ብቻ 250 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን የመሩ 10ኛው አሰልጣኝ በመሆን ድንቅ የረጅም ጊዜ ስኬታቸውን ያረጋግጣሉ።
እ.ኤ.አ በ2019 ታህሳስ ወር ላይ የመድፈኞቹን ሀላፊነት የተረከቡት አርቴታ፣ በጅማሮአቸው ወቅት በርካታ ፈታኝ ሁኔታዎችን ቢያልፉም፣ ክለቡ የሰጣቸውን ሙሉ እምነት እና ጊዜ ተጠቅመው አርሰናልን ወደ ቀደመ ገናናነቱ መመለስ ችለዋል።
በተለይም ባለፈው የውድድር ዘመን ክለቡን ከ22 ዓመታት ረጅም ጥበቃ በኋላ ለፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮንነት ማብቃታቸው የአርቴታን የፕሮጀክት ጥንካሬ ማሳያ ሆኗል።
አርቴታ ለአርሰናል 250ኛ የሊግ ጨዋታቸውን ለማድረግ ሲዘጋጁ የያዙት የማሸነፍ ንፃሬ ከትልልቅ አሰልጣኞች ተርታ አስመድቧቸዋል፡፡
አሰልጣኙ እስካሁን ካከናወኗቸዉ 249 የሊግ ጨዋታዎች 150ዎችን በድል አጠናቀዋል፡፡ 48 ጨዋታዎችን ደግሞ በአቻ ዉጤት ሲያጠናቅቁ በ 51 መርሐግብሮች ሽንፈት አጋጥሟቸዋል፡፡
በዚህም 60 ነጥብ 2 በመቶ የማሸነፍ ንፃሬ አስመዝግበዋል፡፡
በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ በአንድ ክለብ 250 ጨዋታዎችን ካደረጉ 10 አሰልጣኞች መካከል ከአርቴታ የበለጠ የማሸነፍ ንፅፅር ያላቸው ሦስት ታላላቅ አሰልጣኞች ብቻ ናቸው።
እነሱም ፔፕ ጋርዲዮላ (ማንቼስተር ሲቲ) – 70 ነጥብ 8 በመቶ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን (ማንቼስተር ዩናይትድ) – 65 ነጥብ 2 በመቶ እና የርገን ክሎፕ (ሊቨርፑል) – 62 ነጥብ 6 በመቶ በማስመዝገብ ከሚኬል አርቴታ የተሻለ የማሸነፍ ንፃሬ ያላቸዉ አሰልጣኞች ሆነዉ ይገኛሉ፡፡
ዘመናዊ እግር ኳስ በትዕግስት ማጣት እና በፍጥነት አሰልጣኞችን በመቀየር በሚታወቅበት በዚህ ወቅት፣ የ44 ዓመቱ ስፔናዊ አሰልጣን ሚኬል አርቴታ በአርሰናል ያሳዩት ዘላቂነት እና ወጥ ብቃት የቡድኑ ትልቅ ጥንካሬ ሆኗል።
ተፎካካሪ ክለቦች አሰልጣኞችን በመቀየር እና አለመረጋጋት ውስጥ ባሉበት በዚህ ወቅት፣ አርሰናል ከአርቴታ ጋር የጀመረውን የስኬት ጉዞ በማጠናከር በእንግሊዝ እግር ኳስ የበላይነቱን ለማረጋገጥ በሙሉ ዝግጅት ላይም ይገኛል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
የሊቨርፑል እና ኖቲንግሃም ፎረስት ጨዋታ 2 አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቀቀ
ማርሊ ሳልሞን የመጀመሪያውን ፕሮፌሽናል ኮንትራት ፈረመ
ሊቨርፑል ብራድሌይ ባርኮላን ለማስፈረም ከፒኤስጂ ጋር ከስምምነት ደረሰ