“የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የአንድ ተቋም፣ የአንድ ፓርቲ ወይም የአንድ ትውልድ ብቻ ኃላፊነት አይደለም፤ የጋራ ኃላፊነታችን ነው” – ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር)

“የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የአንድ ተቋም፣ የአንድ ፓርቲ ወይም የአንድ ትውልድ ብቻ ኃላፊነት አይደለም፤ የጋራ ኃላፊነታችን ነው” – ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር)

“የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የአንድ ተቋም፣ የአንድ ፓርቲ ወይም የአንድ ትውልድ ብቻ ኃላፊነት አይደለም፤ የጋራ ኃላፊነታችን ነው” ሲሉ በብልፅግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

“ሁሉ አቀፍ እመርታ ለሁለንተናዊ ከፍታ” በሚል መሪ ሀሳብ በብልፅግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ የ2018 በጀት ዓመት ማጠቃለያ እና የ2019 ዕቅድ ግምገማ መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በብልፅግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዲላሞ ኦቶሬ(ዶ/ር)፤ ይህ መድረክ ከህዝቡ የተሰጠንን እምነት በተሻለ አፈጻጸም እና በተጠያቂነት ለመመለስ የሚያስችል ነው ብለዋል።

የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የአንድ ተቋም፣ የአንድ ፓርቲ ወይም የአንድ ትውልድ ብቻ ኃላፊነት አይደለም፤ የጋራ ኃላፊነት ነው ሲሉም ዶ/ር ዲላሞ ገልጸዋል።

የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ጠላትነትን ሳይሆን በሃሳብ መፎካከርን እንዲሁም በሀገር ጉዳይ ላይ በጋራ መቆምን ማዳበር ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ዶክተር ዲላሞ ወጣቶች የነገ መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የዴሞክራሲ እና የሰላም ግንባታው የዛሬ ትልቅ ተስፋዎች በመሆናቸው በሃሳብ፣ በእውቀት እና በውሳኔ ሰጪነት ሊሳተፉ ይገባል ብለዋል።

አክለውም የሴቶች ተሳትፎ ሳይረጋገጥ የተሟላ ዴሞክራሲ ሊታሰብ እንደማይችል አውስተው፣ በፖለቲካው እና በኢኮኖሚው ዘርፍ የሴቶችን አቅም ማጎልበት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የሲቪል ማህበራት በዴሞክራሲ ግንባታ ውስጥ ወሳኝ የህዝብ እና የመንግስት ድልድይ በመሆናቸው፣ ሀገራዊ ሚናቸውን እንዲወጡ አጋዥ መሆን አለብን ብለዋል።

በቀጣዩ የ2019 በጀት ዓመት የዴሞክራሲ እሴቶችን ከማጎልበትና የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት አኳያ ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸው፤ የዴሞክራሲ ግንባታ የሁሉም ዜጋና ተቋም የጋራ ኃላፊነት መሆኑም ጠቁመዋል።

ኃላፊው በንግግራቸው እንዳብራሩት፤ በቀጣዩ ዓመት የዴሞክራሲ እሴቶችን ማጎልበትና ማስረጽ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ሁሉንም ድምጾች ማካተት እንዲሁም ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ጤናማ ፉክክር በማድረግ የጋራ ጥቅም ላይ አብሮ መስራት ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው።

በተጨማሪም የሲቪል ማህበረሰብን አቅም በአግባቡ መጠቀም፣ ወጣቶችን ለቀጣይ የሀገር ግንባታ አመራርነት ማብቃት እና ሴቶችን በፖለቲካና በኢኮኖሚ በማብቃት በውሳኔ ሰጪነት ቦታዎች ላይ እንዲመደቡ ማድረግ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

የውይይት፣ የምክክርና የሰላማዊ ልዩነት አስተዳደር ባህልን ማስፋፋት እና የዴሞክራሲ ተቋማትን በተግባር ማጠናከርም በበጀት ዓመቱ በትኩረት እንደሚሰሩባቸው ኃላፊው አክለው አብራርተዋል።

ዶክተር ዲላሞ “የዴሞክራሲ ግንባታ የትኛውም አንድ ተቋም፣ የአንድ ፓርቲ ወይም የአንድ ትውልድ ብቻ ኃላፊነት አይደለም፤ የጋራ ኃላፊነታችን ነው” በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።

ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የሲቪል ማህበራት እና ህዝቡ ለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ግንባታ የበኩላቸውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ በማቅረብ መድረኩን በይፋ ከፍተዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ አቶ በረከት ከድር በበኩላቸው፤ በ2018 በጀት ዓመት በስኬት የተመሩ በርካታ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን፣ በተለይም 7ኛው አጠቃላይ ምርጫ ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታችን ጠንካራ መሰረት የጣለ እና ኢትዮጵያ ያሸነፈችበት ታላቅ ስኬት መሆኑ አመላክተዋል።

በበጀት ዓመቱ በስኬት ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የወጣቶች እና ሴቶች ክንፍ አደረጃጀቶች በአስተሳሰብ ጥራት እና በተግባር ግንባር ቀደም በመሆን የመሪነት ሚና መጫወታቸው ጎልቶ ታይቷል ብለዋል።

አክለውም መጪውን የ2019 በጀት ዓመት አዲስ ጉልበት እና ግብ ሰጪነት ባለው መልኩ በመጀመር፣ የዘርፉን ስራዎች ወደ ላቀ መዕራፍ ለማሸጋገር የዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ አደረጃጀቶች አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

አቶ በረከት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ማህበራት ለዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ዋና አጋር በመሆናቸው፣ በክፍለ ሀገር እና በዞን/ወረዳ ደረጃ ያሉ ማህበረሰቦችን በንቃት የማሳተፍ ስራዎች በልዩ ትኩረት ይሰራሉ ብለዋል።

የምክር ቤት አባላትን አቅም በማሳደግና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታን በማጠናከር ሂደት ውስጥ የቁልፍ ስራዎች አፈጻጸም በትኩረት የሚከናወን ይሆናል ማለታቸውን ከፓርቲው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።