ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ የተጀመሩ የሌማት ትሩፋት ተግባራትን በተጠናከረ መልኩ  መስራት እንደሚገባ ተመላከተ

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ የተጀመሩ የሌማት ትሩፋት ተግባራትን በተጠናከረ መልኩ  መስራት እንደሚገባ ተመላከተ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 21/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ የተጀመሩ የሌማት ትሩፋት ተግባራት በተጠናከረ መልኩ መስራት እንደሚገባ ተመላክቷል።

በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ ጽ/ቤት “አሻራችን ለትውልዳችን” በሚል መሪ ቃል የ2015 ዓ.ም የክረምት ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ- ግብር በወረዳው ቆንጋ ቀበሌ አካሂደዋል።

በባለፈው ዓመት በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የአካል ጉዳተኞች፣ የአረጋዊያንና አቅመ ደካሞችን ቤት እድሳትና አዳዲስ ቤት የመስራት እንዲሁም ሌሎች ተግባራትን ማከናወናቸውን በመርሃ-ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር የወረዳው ብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ እቴነሽ ጀቦ አንስተው በዘንድሮ ክረምትም ተግባሩን ይበልጥ ለማጠናከር በማቀድ ስራ መጀመራቸውን ገልፀዋል፡፡

የመማር ፍላጎት እያላቸው በገንዘብ እጥረት ከትምህርት ገበታ የሚቀሩ ተማሪዎችን በመለየት የመማሪያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ለማድረግ በማቀድ ወደ ተግባር መግባታቸውንም ወ/ሮ እቴነሽ ገልጸዋል፡፡

የጌዴኦ ዞን ብልፅግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ  ፖለቲካና ርዕዮተ ዓለም ዘርፍ ኃላፊና የጽ/ቤቱ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ በረከት ከበደ እንደገለፁት፤ ሴቶች በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚውና በማህበራዊ ዘርፎች ውጤታማ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል፡፡

በተለይም ከድህነት ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት ከግብ ለማድረስ በጓሮ አትክልት ልማት፣ በፍራፍሬ፣ በወተት ተዋፅዖና በዶሮ እርባታ ስራዎች ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ኃላፊዋ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ውብሸት ኃ/ማርያም – ከፍስሀ ገነት ጣቢያችን