ማህበረሰብ አቀፍ የቲቢ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ሥራ ዘላቂ ውጤት እስኪመዘገብ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

ማህበረሰብ አቀፍ የቲቢ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ሥራ ዘላቂ ውጤት እስኪመዘገብ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 21/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ማህበረሰብ አቀፍ የቲቢ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ሥራ ዘላቂ ውጤት እስኪመዘገብ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ጥሪ አስተላለፈ፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የ2018 አመታዊ የቲቢ፣ ሥጋ ደዌና ሌሎች የሳምባ በሽታዎች ፕሮግራም አፈፃፀም ግምገማና የምክክር መድረክ በጂንካ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትልና የጤና ፕሮግራሞችና ዘርፈ ብዙ ኤችአይቪ መከላከልና መቆጣጠር ዘርፍ ኃላፊ አቶ መና መኩሪያ ከዋና ዋና ተላላፊ በሽታዎች አንዱ ቲቢ ነው ብለዋል።

ቢሮው በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከጤና ሚኒስቴር እና አጋር ድርጅቶች ጋር በጥምረት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፥ በዚህም ከ90 በላይ በሽታውን ለመለየትና መርምሮ ማከም የሚያስችል የተለያዩ የህክምና መሣሪያዎች እንዲሟላ ተደርጓል ሲሉም አቶ መና ገልፀዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትልና በሽታ መከላከልና ጤና ማጎልበት ዋና ዳይሬክተር አቶ መልካሙ ቶንቼ፥ ተላላፊ በሽታዎችን መከላከልና መቆጣጠር ተግባር ቀጣይነት ያለው ሥራን ይጠይቃል ብለዋል።

በመድረኩ የተገኙት በኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትር ቲቢ በሽታዎችና ሌሎች የሥጋ ደዌ በሽታዎች ሀላፊ አቶ ታየ ለታ፥ ቲቢ በሽታ በገዳይነት 7ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፥ በሽታውን ለመቆጣጠር በAI የታገዘና የሚሠራ ዲጂታል ኤክስ ሬይ ተግባራዊ ሆኖ እየተሠራበት ይገኛል ብለዋል።

ከዚህ በፊት በሽታውን መርምሮ ለማወቅ አንድ ወር የሚፈጀውን ጊዜ በአሁን ወቅት ወደ ሁለት ሰዓታት ማውረድ መቻሉን አመላክተው፥ ይህንን በቀጣይ ወደ 30 ደቂቃ ዝቅ ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱንም ሀላፊው አብራርተዋል ።

የመመርመርያ መሣሪያ ግዢ ለመፈፀም ሚኒስቴር መሥሪያቤቱ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር መድቦ ወደ ሥራ መግባቱንም አቶ ታዬ አመላክተዋል ።

የመድረኩ ተሣታፊዎች በቢሮ የሥራ ክፍሎች የሚያቀርቡ ሪፖርቶችን በማድመጥ ምክክር እያደረጉ ይገኛል።

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን