‎የዝናብ እጥረት የቡና ምርትን እንዳይጎዳ የማሳ እርጥበትን መጠበቅ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

‎ሀዋሳ፡ ነሐሴ 22/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በአየር መዛባት ምክንያት እየተከሰተ ያለው የዝናብ እጥረት በቡና ምርትና ጥራት ላይ ተጨማሪ ጉዳት እንዳያስከትል የቡና ማሳዎች በበቂ ሁኔታ እርጥበት እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ።

‎በተለይም የደረሰ ቡናም ሆነ አዲስ የተተከሉ የቡና ችግኞች በቂ ውሃ እንዲያገኙ ማጠጣትና አነስተኛ መስኖዎችን ወደ ማሳ ማስገባት ለዝናብ እጥረቱ የሚሰጥ አስቸኳይ መፍትሔ መሆኑ ተጠቁሟል።

‎በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ250 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ቡና እንደሚለማ ከክልሉ ቡናና ቅመማቅመም ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡናና ቅመማቅመም ባለስልጣን ዳይሬክቶሬት አቶ አማኑኤል ብሩ እንደገለጹት፣ ቡና በክልሉም ሆነ በሀገር ደረጃ የኢኮኖሚ ወሳኝ ምንጭ ቢሆንም፥ ለረጅም ዘመን ምርት ሲሰጥ የቆየ የቡና ተክል እድሜው በመጨመሩ ምርት መስጠት ያቆመ ወይም ምርታማነቱ የቀነሰ ቡና በርካታ ነው።

‎ይህንን ችግር ለመቅረፍም የቡና እድሳት ሥራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን አቶ አማኑኤል ጠቁመዋል። በተለይም FOLUR Ethiopia በጌዴኦ ዞን በሦስት ወረዳዎች የቡና እድሳት ሥራን በስፋት እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

‎በክልሉ ባለፈው ዓመት ከ105 ሺህ ቶን በላይ ቡና መመረቱን የገለጹት አቶ አማኑኤል፥ ከዚህ ውስጥ 46 ሺህ ቶን ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ 32 ሺህ ቶን ብቻ መላኩን ተናግረዋል።

‎ለዚህም የቡና ምርት መቀነስ፣ የዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ ተገማች አለመሆን፣ በአካባቢው የቀይ እሸት ቡና የግዢ ዋጋ መጨመር እንዲሁም አቅራቢ ነጋዴዎች ቡናን በራሳቸው የመያዝ ሁኔታ ከማዕከላዊ ገበያ ጋር አለመጣጣሙ እንደምክንያት ተጠቅሷል።

‎በዘንድሮ ዓመት ከ48 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እቅድ መኖሩን አቶ አማኑኤል ገልጸዋል። የቡና ኢንዱስትሪዎችም ለዚህ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።

‎ሆኖም ከአየር መዛባት ጋር ተያይዞ የዝናብ እጥረት በቡና መልካም እድገትና የፍሬ መሙላት ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን አቶ አማኑኤል አስገንዝበዋል።

‎ቡና በበቂ ሁኔታ እርጥበት ካላገኘ የምርት መጠንን ከመቀነስ ባለፈ በጥራቱ ላይ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ጠቁመው፥ አርሶ አደሩም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት የቡና ማሳዎች በቂ እርጥበት እንዲያገኙ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

‎በተጨማሪም የእሸት ቡና ኢንዱስትሪዎች በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ፣ ቡና በሚገዙበትም ሆነ ከማሳ በሚለቀምበት ወቅት ሙሉ በሙሉ የደረሰውን ቀይ ቡና ብቻ እንዲመርጡ አስገንዝበዋል።

‎ዘጋቢ፡ ውብሸት ካሳሁን – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን