በሁሉም ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶችን በማስቀጠል የምክር ቤት አባላት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 17/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሁሉም ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶችን በማስቀጠል አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ የፀጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ሁሉም የምክር ቤት አባላት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ በደቡብ ኦሞ ዞን የሣላማጎ ወረዳ አስተዳደር አሳስበ።
የወረዳው ምክር ቤት 4ኛ ዙር 10ኛ ዓመት 32ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ አካሂዷል፡፡
የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ህጉ ቅጣቱ አጠቃላይ የወረዳው አስፈፃሚ መስሪያ ቤት የአፈፃፀም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንዳመላከቱት፥ በትምህርት ዘርፍ ከ1ኛ-12ኛ ክፍል ጥቅል ሽፋን በ2018 ዓ/ም በሁለቱም ፆታ 13 ሺህ 528 ተማሪዎችን ለመቀበል ታቅዶ 11 ሺህ 293 ተማሪዎችን በመመዝገብ የቅበላ አፈፃፀሙን 83.47 በመቶ ማሳካት መቻሉን ጠቁመው፥ በዚህም መጠነ ማቋረጥንና መድገምን ለማስቀረት በተሰሩ ሥራዎች ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
በጤናው ዘርፍ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሞችን በማጠናከር የግልና የአከባቢ ጤና አጠባበቅ ሥራን በመተግበር ወቅታዊና የወባ ወረርሽኝ በመከላከል ረገድ ያጋጡሙ ውስንነቶች ቢኖሩም የተሻሉ ሥራዎች ማከናወናቸውን ተመላክቷል።
በተመሳሳይ በግብርናው ዘርፍ በአጠቃላይ በአዝርእትና ሆርቲ-ካልቸር ሰብሎች 24 ሺህ 60 ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ 26 ሺህ 340 በላይ ሄክታር በዘር በመሸፈን ሙሉ ለሙሉ የአረም ቁጥጥር በማድረግ ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉን አመላክተው፥ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሻገር በሚደረገው ጥረት በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረጉ የድጋፍ ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ አስረድተዋል።
በወረዳው በሥራና ክህሎት፣ በህብረት ሥራና ሌሎችም ዘርፎች የተመዘገቡ አመርቂ ውጤቶች የጋራ ጥረት ስኬቶች ስለመሆናቸው አመላክተዋል።
በቀረበው የአፈፃፀም ሪፖርት መነሻ ከምክር ቤት አባላት በአርብቶ አደሩ አከባቢ የሆስቴል አዳሪ ትምህርትን ማጠናከር በጤናው ዘርፍ የጤና ኤክሰቴንሽን ሥርዓትን ማጠናከርና ማሰልጠን፥ በግብርናው ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሻገር ድጋፍን ማጠናከር እና ሠላሙን በሠላሙ ጊዜ መስራት የሚሉትና ሌሎችም ዋና ዋና ጉዳዮች ተነስተዋል።
ከመድረኩም መንግስት ከያዘው የትምህርት ጥራት አኳያ ውጤታማ ተማሪዎችን በሆስቴል አዳሪ ት/ቤት አቅፎ ለማሰተማር እየሰራ መሆኑን አመላክተው፥ አስተዳዳሪው የጤና ኤክስቴንሽን ሥርዓትን ማጠናከርና ማሰልጠን የሚለው ጥያቄ ተገቢ መሆኑን አምነው በቀጣይ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ከሁሉ በላይ በዋናነት በሁሉም ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶችን በማስቀጠል ለልማትና መልካም አስተዳደር ሥራዎች ማነቆ በመሆን እየተፈታተነ ያለውን የፀጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ማህበረሰቡን ያሳተፈ የፀጥታ ሥራ መስራት ላይ ምክር ቤቱ በመደገፍ የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ ዋና አሰተዳዳሪው አሳስበዋል።
ዘጋቢ: ከተማ በየነ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
የአርሶ አደሩን የመሬት ሀብት ከፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ጋር በማስተሳሰር አርሶአደሩ የፋይናንስ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ጤና ቢሮ የእናቶች ጤናና የሥርዓተ-ምግብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የ2018 ባጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም መድረክ በሆሳዕና ከተማ እያካሄደ ይገኛል
የከተማ አስተዳደሩ ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽህፈት ቤት ወጣቶችን በማህበር በማደራጀት የኢኮኖሚ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ