የከተማ አስተዳደሩ ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽህፈት ቤት ወጣቶችን በማህበር በማደራጀት የኢኮኖሚ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ

የከተማ አስተዳደሩ ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽህፈት ቤት ወጣቶችን በማህበር በማደራጀት የኢኮኖሚ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ

ወጣቶችን በማህበር በማደራጀት የኢኮኖሚ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ እያደረገ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀዲያ ዞን የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ስራ ዕድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽህፈት ቤት ገልጿል፡፡

በከተማው በተለያዩ የስራ ዘርፎች የተሰማሩ ወጣቶች ውጤታማ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ስራ ዕድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ እና የስራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ተመስገን ወርቁ እንደገለፁት፤ በከተማ አስተዳደሩ በ2018 በጀት ዓመት ከ16 ሺህ 6 መቶ በላይ ስራ አጥ ወጣቶችን በመለየት የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል።

እነዚህ ወጣቶች በኢንዱስትሪ፣ በከተማ ግብርና እንዲሁም በአገልግሎት ዘርፎች መሠማራታቸውን ያስረዱት ኃላፊው፤ ከእነዚህም ውስጥ 96 በመቶ የሚሆኑት ቋሚ የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

ወጣቶች ከተደራጁ በኋላ መንግሥታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የፋይናንስ ምንጮችን በማመቻቸት ወደ ተግባር መግባታቸውን አቶ ተመስገን ገልጸዋል።

በ2019 በጀት ዓመትም ከ18 ሺህ 9 መቶ በላይ ስራ አጥ ወጣቶችን በመለየት የስራ ዕድል ለመፍጠር ዕቅድ ተይዞ እንቅስቃሴ መጀመሩንና አስፈላጊ ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግም አመላክተዋል።

ለወጣቶቹ የመስሪያና መሸጫ ቦታ በማመቻቸት፣ የማምረቻ ግብዓት አቅርቦትና የገበያ ትስስር ከመፍጠር አንጻር ትኩረት እንደሚደረግ የገለፁት አቶ ተመስገን፤ ከ90 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ ለብድር ስርጭት መያዙንም አስታውቀዋል።

በሆሳዕና ከተማ በወጣቶች ስብዕና ግንባታ ማዕከል ውስጥ ”ናቹራል ካፌ” በሚል ስያሜ ለአምስት ተደራጅተው በአገልግሎት ዘርፍ የተሠማሩ ወጣቶች በስራቸው ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የማህበሩ ሰብሳቢ ወጣት ይርጋ ፍቃዱ፤ ማህበሩ በ2017 በጀት ዓመት ማብቂያ አካባቢ በአንድ መቶ ሺህ ብር ካፒታል ስራ የጀመረ ሲሆን በአሁን ሰዓት የኢኮኖሚ አቅሙን እያጎለበተ መምጣቱን ተናግሯል።

ማህበሩ በስራው የበለጠ ስኬታማ ለመሆን የሚያስችሉ እሴቶችን በመጨመር የወደፊት ራዕይ ሰንቆ እየተጋ ነውም ብሏል ሰብሳቢው።

ሌላው የ”ውሃ ልማት ኢንተርፕራይዝ ብሎኬት እና ቴራዞን ማምረቻ ማህበር” አስተባባሪ በለጠ ደገፈ፤ በ2017 በጀት ዓመት ለአምስት ተደራጅተው የጀመሩት ስራ ውጤታማ በመሆን በአሁኑ ወቅት 85 ለሚሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ተጨማሪ የስራ ዕድል መፍጠሩን ተናግሯል፡፡

ማህበሩ ለኮሪደር ስራ የሚያስፈልጉ ቴራዞዎችንም ሆነ ለተለያዩ ግንባታዎች የሚሆኑ ብሎኬቶችን በማምራት ከሌሎች አካባቢዎች ለማምጣት የሚወጣውን ወጪ፣ ጉልበትና ጊዜ ብክነት ማስቀረቱን ገልጾ፤ ዘመናዊ ማሽነሪዎችን ከሀገር ዉጪ በማስገባት ዘርፉን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ዝግጅት ማድረጉን አብራርቷል።

ወጣቶቹ አክለው በሰጡት አስተያየት፤ በህገወጥ መንገድ ስራ ፍለጋ በማለት ለስደት በሚሊዮኖች የሚገመት ብር የሚያባክኑ ወጣቶች ያላቸውን ገንዘብ ይዘው በነፃነት በሀገር ሰርተው ለመለወጥ በቂ መነሻ እንደሚሆንላቸው አንስተው ወጣቱ ትውልድ በነቃ ስሜት ወደ ስራ ሊመለስ ይገባል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ: መንግስቱ ፊጣሞ – ከሆሳዕና ጣቢያችን