ቶተንሃም ሳቪንሆን በ85 ሚሊዮን ፓውንድ ለማስፈረም ከስምምነት ደረሰ

ቶተንሃም ሳቪንሆን በ85 ሚሊዮን ፓውንድ ለማስፈረም ከስምምነት ደረሰ

ቶተንሃም ሆትስፐር የ22 አመቱን ብራዚላዊ የክንፍ መስመር ተጫዋች ሳቪንሆን ከማንቸስተር ሲቲ ለማስፈረም ከስምምነት ላይ መድረሱ ተመላቷል።

ስፐርሶች ለተጫዋቹ ዝውውር አስቀድመው 75 ሚሊዮን ፓውንድ የሚከፍሉ ሲሆን፣ ከተጫዋቹ ስኬታማነት ጋር የሚያያዝ ተጨማሪ 10 ሚሊዮን ፓውንድ (በጠቅላላ £85 ሚሊዮን ፓውንድ) ለመክፈል ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ተጫዋቹ ወደ ሰሜን ለንደን አምርቶ የረጅም ጊዜ ውል ከመፈረሙ በፊት የህክምና ምርመራውን እንደሚያደርግ ተገልጿል።

ሳቪንሆ ወደ ቶተንሃም የማምራት ሂደት ከአንድ አመት በላይ የወሰደ ሲሆን፣ ስፐርሶች ባለፈው የክረምት ዝውውር መስኮት እሱን ለማስፈረም ያቀረቡት ጥያቄ ሳይሳካ ቀርቶ ነበር።

ተጫዋቹ በኢቲሃድ ለመቆየት ቢመርጥም፣ ባለፈው የውድድር ዘመን በፔፕ ጓርዲዮላ ስር በፕሪሚየር ሊጉ በቋሚነት መሰለፍ የቻለው በ7 ጨዋታዎች ላይ ብቻ በመሆኑ በቂ የመጫወት እድል አላገኘም።

የቶተንሃሙ አሰልጣኝ ሮቤርቶ ዲ ዘርቢ ቀደም ሲል አማካኝ መስመራቸውን በማጠናከር ማቴዎስ ፈርናንዴዝን ከዌስትሃም እና ሳንድሮ ቶናሊን ከኒውካስል በድምሩ በ185 ሚሊዮን ፓውንድ ማስፈረማቸው ይታወሳል።

አሁን ደግሞ ትኩረታቸውን ወደ አጥቂ መስመር በማዞር የሳቪንሆን ዝውውር አጠናቀዋል።

የቶተንሃም የዝውውር እንቅስቃሴ በዚህ ብቻ የሚያበቃ አይመስልም።

ቢቢሲ ስፖርት እንደዘገበው ከሆነ ስፐርሶች የሳቪንሆ የቡድን አጋር የሆነውን ግብጻዊውን አጥቂ ኦማር ማርሙሽን ለማስፈረም የሚያደርጉት ንግግር በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል።

በ2025 ከፍራንክፈርት በ59 ሚሊዮን ፓውንድ ሲቲን የተቀላቀለው ማርሙሽ፣ ባለፈው የውድድር ዘመን የመሰለፍ እድሉ አነስተኛ ነበር።

የሳቪንሆ ዝውውር ቶተንሃምን በክረምቱ የዝውውር መስኮት ያወጣውን ወጪ ከ300 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ያደርሰዋል።

ሆኖም ክለቡ ክርስቲያን ሮሜሮ፣ ጅድ ስፔንስ እና ሉካ ቩስኮቪችን በመሸጥ ወደ 140 ሚሊዮን ፓውንድ ገቢ ማግኘት ችሏል።

ቶተንሃም የኢንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታውን በነገው ዕለት ከብሬንትፎርድ ጋር የሚያደርግ ሲሆን፣ ማንቸስተር ሲቲ በበኩሉ እሁድ ቦርንመዝን ያስተናግዳል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ