የቱርሚ ወይጦ ኮንክሪት አስፋልት የግንባታ ሥራ በተያዘለት ጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ተጠየቀ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 21/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ኦሞ ዞን የቱርሚ ወይጦ 120 ኪሎ ሜትር የኮንክሪት አስፋልት ግንባታ ሥራ ያሉበት ችግር ተፈትቶ በተያዘለት ጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ተጠየቀ።
የደቡብ ኦሞ ዞን ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በስፍራው ተገኝተው የመንገድ ግንባታው ያለበትን ደረጃ ተመልክተዋል።
የቱርሚ – ወይጦ ኮንክሪት አስፈልት መንገድ ግንባታ በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ተቆጣጣሪነት፥ በራማ ተቋራጭ በ2013 ዓ.ም ውል መግባቱን ተከትሎ ስራው መጀመሩን የራማ ግንባታ ተቋራጭ የወይጦ – ቱርሚ መንገድ ፕሮጀክት ሥራ አስኪጅ ኢ/ር አዲስ አጋፋሪ አስረድተዋል።
ግንባታውን በአራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ለማስረከብ ውል ቢገባም በኢንዱስትሪ ግብዓት እጥረት፣ በካሳ ክፍያና ግንዛቤ እጥረት ምክንያት የግንባታ ሂደቱ ሊዘገይ ችሏል፡፡
እስካሁን ባለው አፈጻጸም 21 ነጥብ 35 በመቶ መድረሱን የጠቆሙት ኢ/ር አዲስ፥ የተጠቀሱ ችግሮች ከተፈቱ በቀሪ ጊዜያት የመንገዱን ግንባታ ለማጠናቀቅ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የጂንካ አካባቢ ፕሮጀክቶች ሥራአስኪያጅ አቶ ብርሃኑ መሸሻ መንገዱ ግንባታ በውሉ ጊዜ እየሄደ አለመሆኑና መጓተት መኖሩን ይናገራሉ።
ምንም እንኳ የተጠቀሱ ችግሮች ቢኖሩም፥ የግንባታውን ሂደት ጥራቱን ጠብቆ መንገዱን ማጠናቀቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የመንገዱ ግንባታ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው የገለፁት የሐመር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፎራ ጋርሾ፥ ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር በመፍታት ከአካባቢው ማህብረሰብ ጋር የጋራ መገባባት በመፍጠር የመንገዱ ግንባታ እንዲጠናቀቅ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
የመንገዱ ግንባታ በስፍራው በመገኘት ምልከታ ያደረጉት የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ፥ በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በዞኑ ሦስት የመንገድ ሥራዎች እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከቱርሚ – ወይጦ 120 ኪሎ ሜትሩ ትልቁ የመንገድ ግንባታ እንደሆነ ያስረዱት ዋና አስተዳዳሪው መንገዱ ከዞኑ አልፎ ከኬኒያ ጋር ለመገናኘት ብሎም በዞኑ እየተገነቡ ካሉ ትላላቅ ሜጋ ፕሮጀክት የሚመረቱ ምርቶችን ለማውጣት ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት መሆኑን አመልክተዋል።
ለአካባቢው ማህብረሰብ ለውጥ ትልቅ ዕድል ይዞ የሚመጣ መንገድ በመሆኑ የሚነሱ ጥቃቅን ችግሮች እንዲፈቱ ተደርጎ የመንገዱ ግንባታ ለአፍታም ያህል ሳይቋረጥ እንዲጠናቀቅ ይደረጋል ብለዋል ዋና አስተዳዳሪው።
ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ