የተስተካከለ የአየር ንብረት እንዲኖር ችግኞችን የመትከል ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 20/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሁሉም አካባቢ የተስተካከለ የአየር ጸባይ እንዲኖር ለማስቻል ችግኞችን የመትከል ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ።
የደቡብ ኦሞ ዞን ከፍተኛ አመራሮች ቆላማ አካባቢ በሆነው ሐመር ወረዳ ቱርሚ ከተማ አስተዳደር በመገኘት ችግኝ ተክለዋል።
በተከላ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ ለአካባቢው ምቹ ስነምህዳር ያላቸውን ችግኞችን የመትከል ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
ሐመር ወረዳ ቱርሚ ከተማና አካባቢ ሞቃታማና ቆላማ የአየር ፀባይ ያለበት ሲሆን ለአካባቢው ምቹ የሆኑ ችግኞች መተከላቸውን ዋና አስተዳዳሪው ገልፀዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው የአንድ ቀን ጀምበር አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እንደዞን ከ1 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን አቶ ንጋቱ አስታውሰው ተግባሩ በሁሉም አካባቢ የክረምት በጎ ፈቃድ መርሐ ግብር ጭምር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
እንደዓለም ያለውን የአየር ብክለትና ተጽእኖ ለማስቀረት ችግኝ መትከልና የአካባቢ ጥበቃን ማረጋገጥ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ስለመሆኑም ዋና አስተዳዳሪው አስገንዝበዋል።
በቱርሚ ከተማ አስተዳደር በነበረው ተከላ መርሐ ግብር የተሳተፉ አካላትም አካባቢው ሞቃታማ በመሆኑ ለሰው ልጆችም ይሁን ለእንስሳት የአካባቢ ጥበቃ ወሳኝ በመሆኑ ችግኞችን እየተከሉ አንደሚገኙ ገልፀው የተተከሉት ችግኞችም ፀድቀው ለተፈለገው አላማ እንዲውል እንደሚንከባከቡም አረጋግጠዋል ።
ዘጋቢ: ተመስገን አበራ-ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
ውድና ውስን የሆነውን መሬት ያለብክነት ለመምራትና ለመጠቀም እየተሰራ ነው – የባስኬቶ ዞን አስተዳደር
በጎፋ ዞን ጋልማ ከተማ በ2019 በጀት ዓመት ከ18 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱ ተገለፀ
የሀድያ ብሔር የዘመን መለወጫ “ያሆዴ” በዓልን ለማክበር በቂ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ