በክልሉ 295 የቱሪዝም መዳረሻዎችን በመለየት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሰኔ 24/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በጊቤ ሸለቆ ብሄራዊ ፓርክ የማህበረሰብ አቀፍ ሎጅ ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ አኖረ፡፡
በክልሉ 295 የቱሪዝም መዳረሻዎችን በመለየት እየተሰራ መሆኑንም ቢሮው አስታውቋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትልና የቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ አቶ መሐመድኑር ሳሊያ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት በክልሉ 295 የቱሪዝም መዳረሻዎችን በመለየት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በክልሉ የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት አለም አቀፍ መመዘኛዎችን እንዲያሟሉ በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑም አቶ መሐመድኑር አስረድተዋል።
የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ ከሃገሪቱ መዲና አዲስ አበባ በቅርብ ርቀት የሚገኝ በመሆኑ አስፈላጊውን የመሠረተ ልማት በሟሟላት ለቱሪስት መዳረሻ የማድረግ ስራ እንደሚሰራ አቶ መሐመድኑር ጠቁመዋል።
አክለውም ፓርኩን የቱሪስት መዳረሻ ከማድረግ በተጨማሪ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር ለአካባቢው ማህበረሰብ የስራ እድል ትስስር እንዲፈጠርና የቱሪዝም ፍሰት እንዲፋጠን ይሰራል ብለዋል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ የጉራጌ ማህበረሰብ ተፈጥሮውን ጠብቆ የሚኖር ሕዝብ እንደሆነ ገልጸው፣ የማህበረሰቡ አኗኗርና ባህልም ራሱ የቱሪዝም መስህብ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለአብነትም የጉራጌ ባህላዊ የገጠር ቤት አሰራርና የጉራጌ ጀፎረ፣ ሌሎች ቅርሶችና እሴቶች የአካባቢውን የቱሪዝም ሀብቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።
አቶ ላጫ አክለውም ከመንግስት ጥረት ባሻገር የግሉ ዘርፍ ባለሀብቶችም በፓርኩ ውስጥ የመስተንግዶና የቱሪዝም መሠረተ ልማቶችን በመገንባት ተሳትፎአቸውን ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
ፓርኩ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብቸኛ ፓርክ በመሆኑ ክልሉ የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶችን በልዩ ትኩረት በማሟላት ፓርኩን እንዲያለማ በማመላከት የአካባቢው ማህበረሰብ ፓርኩን በአግባቡ በመጠበቅና በልማቱ ውስጥ በንቃት በመሳተፍ የቱሪዝም ዘርፉ የዘላቂ ልማትና የገቢ ምንጭ እንዲሆን የራሱን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።
የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ መስፍን ተካ በበኩላቸው፤ የጊቤ ሸለቆ ብሄራዊ ፓርክ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት በጉራጌ ዞን ውስጥ በሚገኙ 4 ወረዳዎች ማለትም አበሽጌ፣ ቸሃ፣ እኖር እና እኖር ኤነር መገር ወረዳዎች ውስጥ ባሉ 23 ቀበሌዎች እንደሚያዋስኑት ተናግረዋል።
የብሔራዊ ፓርኩ አጠቃላይ ስፋት 36000 ሄክታር የሚሸፍን እና ከመዲናችን አዲስ አበባ 178 ኪሎ ሜትር እና ከወልቂጤ ከተማ 18 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደሚገኝ በመጥቀስ
በብሔራዊ ፓርኩ ውስጥ ከ12 በላይ አመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞች፣ ለእይታ ማራኪ መልክዓ ምድር መኖሩን ያነሱት አቶ መስፍን ትላልቅ አጥቢ የዱር እንሰሳት፣ አእዋፋት፣ በውሃ ውስጥ የሚኖሩ የዱር እንሰሳት፣ የእጽዋት ዝርያዎች እንዲሁም ሌሎች የቱሪዝም መስህቦች ይገኛሉ ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ ከክልል፣ ከዞንና ከወረዳ የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡ ፍስሀ ክፍሌ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
የሀለባ ዞን ምክር ቤት ለ2019 በጀት ዓመት ከ3 ቢልዮን 293 ሚልዮን ብር ባለይ በጀት አጸደቀ
መስራት እየቻሉ የገንዘብ እጥረት የገጠማቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ችግሮች ለመፍታት የህብረት ስራ ማህበራት ሚና ቀላል አለመሆኑ ተገለጸ
በስልጤ ልማት ማህበር ለ3ኛ ጊዜ በተዘጋጀው የችግኝ ተከላ መርሀግብር ከሀገር ውስጥና ከውጪ ሀገር የተሰበሰቡ የአካባቢው ተወላጆች በዞኑ በሚገኙ የላንፉሮ ወረዳና ጦራ ከተማ አስተዳደር ችግኞችን ተክለዋል ።